Adama Land Management Development Agency
Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Adama Land Management Development Agency, Adama.
08/09/2025
ይድረስ ለመጅሊስ አመራሮች!
🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴🔴
በአሕመዲን ጀበል
💥💥💥💥💥💥
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት(መጅሊስ) ምርጫ ከነጠንካራና ደካማ ጎኖቹ በትናንትናው እለት ተጠናቋል። የመጀመሪያው ጠንካራ ጎኑ ምርጫ የሚባለው ነገር ራሱ አጀንዳ መሆን መቻሉና ምርጫው መካሄዱ ነው። ሌላኛው ደግሞ የመሪነት ግንዛቤንና የመመረጥ ባህልን በሕዝባችን ዉስጥ በማስረጽ ረገድ እርሾ ማኖር መቻሉ ነው።በእርግጥ በርካታ ስፍራዎች ላይ ቅሬታ የፈጠሩ አካሄዶች እንደሚኖሩ ብረዳም ቅሬታ መፈጠሩ ራሱ መሪን በመምረጥ መብትና አካሄድ ዙሪያ በመሆኑ አጀንዳው ራሱ መከፈቱ መልካም ነገር ነው። ምክንያቱም ቅሬታዎች መፈጠራቸው በራሱ ለቀጣይ እርምትና ትግል መነሻ ይሆናሉና። በተጨማሪም በአንዳንድ አከባቢዎች ላይ ደግሞ እጩ ሆነው ለቀረቡ ሰዎች ሕዝቡ «ለሙስሊሙ ምን ሠራችሁ? » በሚል መጠየቅ መጀመሩን መስማቴ ነው።
ቋሚ ሊሆን ይገባዋል!
📣📣📣📣📣📣
ሌላኛው በዚህ ምርጫ የታየው ወሳኙ ጥቅም የመስጂዶችን፥ የኢማሞች፥ የተመዝጋቢዎችን መረጃ ለመመዝገብ መሞከሩ ነው። በይፋ እንደተገለጸው በዚህ ምርጫ 13 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንደተመዘገቡ ተጠቅሷል። አሃዙ የተጋነነ ቢመስልም አብዛኛውም በማኑዋል(በወረቀት ላይ) ነው የተመዘገቡት ቢባልም ጅምሩ በራሱ ትልቅ ነው። በተለይ ደግሞ በመላ ሀገሪቱ ምርጫ ተካሄደባቸው የተባሉባቸው 49 ሺህ መስጂዶች እያንዳንዳቸው በወረቀት ላይ የሰበሰቧቸው መረጃዎች በሙሉ ማንኛውንም መስዋእትነት ተከፍሎበት አንድም ሳይቀር መረጃዎቹን ከወረቀት ወደ ዳታቤዝ ሲስተም ማስገባት ይገባል።
ይህ ተግባር ራሱ ከምርጫው ከራሱ የበለጠ ጠቀሜታ ያለው ተግባር ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ መስጂድና የምርጫ ጣቢያ ከዚህ በፊት በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ሲሰራባቸው የነበሩትን መረጃዎችን የመሰብሰብን ተግባርን ማስቀጠል ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትልቅ ዉለታ መዋል ነው። የመጅሊስ አመራሮችም ሆኑ የመስጂድ አስተዳደሮች ጭምር ትኩረት በመስጠት ከምርጫው በኋላም ሊቀጥል ይገባል። ደካማ ጎኖቹ ደግሞ በሚገባ ተመዝግበውና በቂ ዉይይት ተደርጎባቸው ተሰንደው ለቀጣዩ ልንማርባቸው ይገባል።
በተለይ የምርጫው አስፈጻሚ አካላት ይህን ሳይሰሩ በሁሉም ስፍራ ሊበተኑ አይገባም። ይህ ሳይሰራ ስራቸውን እንዳ ጠናቀቁ ከቆጠሩ ትልቅ ኪሳራ ይሆናል። ስለሆነም የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ቋሚ የሚሆንበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል። በተለይም ጽ/ቤተ ከሚሰራቸው ሥራዎች መካካል የተሰባሰቡ መረጃዎችን በማደራጀትና በመተንተን በተጨማሪ እያንዳንዱ ሙስሊም የመጅሊስ አባል ሆኖ የሚመዘገብበት ስርዓት ከዳር መድረስ ይገባዋል።
ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ምርጫዎች ተቋሙ በሐጅ ገቢ ላይ ከመንጠልጠን በመላቀቅ በሀገር ደረጃ ለተመራጮችና ሠራተኞቹ በሙሉ ደሞዝ ከፍሎ ማሰራት እንዲችል እያንዳንዱ ሙስሊም ለተቋሙ ቋሚ የአባልነት ወርሃዊ ክፍያ መክፈል ሲችል ብቻ መምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት ሊያገኝ ይገባል። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሙስሊም ግዴታውን ሳይወጣ ስለመብትና መልካም አግልግሎት ማውራት አግባብ አይደለምና።
ቅጥረኞች ናችሁ!
💢💢💢💢💢
በናንተ እና በሕዝቡ መካከል ያለው ግንኙነት የአገልጋይና የተገልጋይ፥ የመሪና የተመሪ፥ የቅጥረኛና የቀጣሪ ነው። አለቃችሁ የተቋሙና የመብቱ ባለቤት ሕዝቡ ነው። የእያንዳንዳችሁ መብት በተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተለይቶና ተቆጥሮ የተሰጣችሁ ያክል ብቻ ነው። የናንተ ሚና የወካይነት ነው። የወኪል ስልጣን ወካዩ የወከለውን ያክል ብቻ ነው። ወካይ የተወካይን ስልጣን በፈለገው ጊዜ መሻር እንደሚችልም አትርሱ። በሕጉ ባይጻፍ እንኳ ለአምስት ዓመታት የተሰጣችሁ ዉክልና ወካዩ ሕዝብ በፈለገው ጊዜና ሰዓት የመሻር ስልጣን እንዳለው ለአፍታም ቢሆን አትርሱ። ሌላው ቢቀር ሕዝቡ ከቢሮ ባያወጣችሁ እንኳ ከልቡ ሊያወጣችሁ እንደሚችልም አትርሱ።
አብዛኛው ሕዝብ የወከለውን አካል ጥቂቶች በራሳቸው ፍላጎት ዉክልናውን ተላልፈው ከተወካይነት ለማውረድ ሲሞክሩ አመጻ እንደሚሆነው ሁሉ ወካይም በተወከለበት ሳይገኝም አብዛኛው ሕዝብ አትወክለኝም እያለ ዉክልናውን አሳልፌ አልሰጥም ብሎ የታገለ መሪም በሕዝቡ መብት ላይ ድንበር የተላለፈ አመጸኛ ነው። እናንተ ለሕዝቡ ጥቅምና ጉዳይ በተግባር ስትቆሙ ሕዝቡ ታዘዘን ሳትሉ ሲታዘዛችሁ ታያላችሁ። መሪን መታዘዝ ግዴታ እንደሆነው ሁሉ የሕዝቡን ጥቅም፥ መብትንና ፍላጎትን መጠበቅም ግዴታችሁ ነው።
ተጠያቂነትን አስፍኑ!
🍁🍁🍁🍁🍁🍁
ከምርጫው በፊት ከመሪነት ጋር ተያይዞ በርካታ ነጥቦችን አንስቻለሁ። ቁልፍ ጉዳዮች መሪዎችና ሕዝቡ የመሪነትን ምንነት ተረድተው ተገቢውን ትኩረት በመቸር መሪን ከመምረጥ እስከ መርቶ ዉጤት ማምጣት ኃላፊትን በተግባር መወጣት ነው። መሪነት አደራ(አማና) ነው። አደራ ተጠያቂነትን ያስከትላል። ተጠያቂነት ላይ ደግሞ መውደቅም አለ።
አደራን በመወጣት በወደቃችሁ ጊዜ ማንም ይሁን ማን ከአላህ ቅጣት አያድናችሁም። የምትጠየቁት በሰራችሁት ብቻ ሳይሆን መስራት እየቻላችሁና መስራት ሲገባችሁ ባልሰራችሁት ጭምር ነው። ሌላው ለአፍታም ቢሆን መሳት የሌለባችሁ የአመራራችሁ መሠረት ፍትህ ይሁን። በራሳችሁም፥ በቤተሳበችሁም፥ በወገናችሁም ሆነ በማንኛውም የሰው ልጅ ጉዳይ መመሪያችሁ ፍትህ ብቻ ይሁን። የተጠያቂነት አስኳሉ ፍትህን ማጉደል ነውና።
የተቋም የጥንካሬ ምንጭ የሥራ ድርሻ፥ ወሰንና ሚናዎች ግልጽ በመሆናቸው ላይ ነው። ሁሉም በተሰጠው ድርሻና ኃላፊነት ልክ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል።
የመሪነት ሚና ጎልቶ የሚታየውም በተቋሙ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን በመቻል ላይ ነው።መጅሊስ በታሪኩ ተጠያቂነትን ጋር ብዙም አይተዋወቁም። ከነበረም በታችኞቹ ሠራተኞች ደረጃ ነው።በበርካታ ሙስናና ብልሹ አሰራር ተተብትቦ ሳለ ጥፋተኞች ተጠያቂዎች ሲሆኑ አይታይም ነበር። ተጠያቂነትን ለማስፈን አመራሮቹ እነርሱም ሆኑ እያንዳንዱ ሠራተኛ ቢያንስ በሥራ ቀናት ለስምንት ሰዓታት በሥራ ገበታቸው ላይ ሳይገኙ ደሞዝ ከመውሰድ መቆጠብ ይገባቸዋል።ስምንት ሰዓት ደሞዝተኛ ስለሆኑ የግድ ከነርሱ የሚጠበቅባቸው ሲሆን እንደ ዲን ተቆርቋሪነትና ለተቋም እንደ ሚያስብ ሰው ደግሞ ከዚያ በላይ ጊዜ ሊሰጡ ይጠበቅባቸዋል።
ተጠያቂነትን ለማስፈን ሁሉ ነገር በአመራሩ ጫንቃ ላይ የተንጠለጠለ ሊሆን አይገባውም። ነገር ግን ራሱን የቻለ ጉድለትና ስህተት፥ ክፍተትና ብክነትን፥ ኃላፊነትን አለ መወጣትን የሚጠየቅበትን ስርዓትን መፍጠር ይገባል። ለዚህ ደግሞ አመራሮቹ ራሳቸው ለሕግና ሥርዓት ተገዢ በመሆን በተግባር መሪም ቢሆን ከተቋም በታች መሆናቸውን በሕግ አግባብ እነርሱን እንዲቆጣጠር ሥልጣን ለተሰጠው አካልና አሰራር በመገዛት በተግባር በማስመስከር ነው።በዚህ ረገድ የተቋሙ አካል ያልሆኑ የመሪዎች ቤተሰቦችና ዘመዶች በተቋሙ ጉዳይ አንዳች ሚና እንደሌላቸው በተግባር በማስመስከር ጭምር ይጠይቃል።
እያንዳንዱ ሠራተኛ ሚናውንና ኃላፊነቱን በግልጽ የሚያውቅበት ፥ የተቋሙን መተዳደሪያ ደንብና የዉስጥ ፖሊሲዎችንና ማኑዋሎችን በሚገባ አውቆና ቃል በቃል ሸምድዶ መንቀሳቀስ እንዲችል ማድረግ ተጠያቂነትን ከማስፈን ሊቀድም ይገባል። ይህ ሲሆን ነው እያንዳንዱ አካል በሚገባ የሥራ አፈጻጸሙ ሊገመገም የሚችለው።
ዉዳሴ መርዝ ነው!
🍅🍅🍅🍅🍅🍅
ከማንም ከምንም በፊት አላህን ለማስደስት ጣሩ። የቆማችሁት ለሕዝበ ሙስሊሙና ተቋሙ እስከ ሆነ ድረስ የሕዝበ ሙስሊሙን ጥቅምና ጉዳይን ከራሳችሁም፥ ከቡድናችሁም ሆነ ከመንግስት ጥቅም አስቀድሙ። መሪ፥ ፕሬዝዳንት፥ ጸሐፊ፥ሙፍቲ ወዘተ የሚሉ ቅጽሎች እንዳ ያሳስታችሁ። የመሪነት አማናን ስትቀበሉ የተቀበላችሁት ለማገልገል ነው። ለማግልግል አደራ የተቀበለ አካል ደግሞ አገልጋይነቱን ፈጽሞ ሊረሳ አይገባውም። የምታዙበትን ጥቅም በመፈለግ አልያም ችግር ታደርሱብኛላችሁ ብሎ በመስጋት እውነታውንም ሆነ የናንተን ጉድለትና የአመራራችሁን ክፍተት ላይነጋራችሁ ይችላል። ጥቅም ባለበት ሁሉ እያስተዋሉ ለመቋደስ የሚያሞግሱ በበዙበት ጊዜ በምትሰሙት ተታላችሁ ራሳችሁን አጉል ከኮፈሳችሁ አወዳ ደቃችሁ ይከፋል። ስልጣንን ማገልገያ ሳይሆን መገልገያ ፥ የሕዝብ አገልጋይ ሳይሆን የሕዝብ አለቃ፥ እናንተ መጠየቅ እንጂ መጠየቅ የሌለባችሁ አድርጋችሁን ራሳያችሁ ወደ ማየት ታመራላችሁ። ያኔ በዉዳሴ መርዝ የተመረዛችሁ ያናንተ ነገር በጸጸት ካልተመለሳችሁ በቀር የጊዜ ጉዳይ ቢሆን እንጂ ፍጻሜያችሁ የከፋ እንደሚሆን እሙን ነው።
እውነተኛና ጠቃሚ ምክር ማግኘት ከፈለጋችሁ ራሳችሁን በጥቅም ፈላጊዎች አትክበቡ። ምክንያቱም ከእናንተ አንዳች ፈላጊዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት እውነቱን እያወቁ የማይናገሩት፥ ጉድለታችሁን እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉበት እድላቸው ሰፊ ነው።ሌሎች ደግሞ የሚፈልጉትን ለማግኙት በፍላጎታችሁ ሊገቡባችሁ ይችላሉ። የምትወዱትን ካወቁ የምትወዱትን እየነገሯችሁ የሚወዱትን ታደርጉለችሁ ይጥራሉ።በነዚህ ዓይነት ከጃይ ሰዎች ራስን መክበብ ከእውነታው የራቀ ከንቱ ዉዳሴ እያቀረቡ እውነቱን ከማየት እንድትታወሩ ያደርጓችኋል።
ዉዳሴ እንደ ጨዋማ ዉሃ ነው!
✈✈✈✈✈✈✈✈✈
ስለራሱ ዉዳሴ መስማትን ሱስ ያደረገ መሪ እርካታ የለውም። እንደ ጨዋማ ዉሃ ነው። በጠጣው ቁጥር ይበልጥ ይጠማዋል። ጨዋማ ዉሃ ጥምን እንደማይቆርጠው ሁሉ መፍትሄው በዉዳሴ ያልተበረዘ እውነትን መስማት እንጂ ከንቱ ዉዳሴውን መጋት እይደለም።
ማድመጥ የምትወዱት ስህተታችሁን የማይናግሯችሁንና በስህተታችሁ ተቃውሞ የማያቀርቡ ሰዎችን ብቻ ሲሆን፥ በናንተ ቢሮም ሆነ አመራር ዉስጥ አጨብጫቢዎችና ቲፎዞዎች በቀላሉ ማፍራት ትችላላችሁ። እውነተኛ የሥራ ባልደረባን ሳይሆን መስማት የሚሻውን እየመረጡ የሚግቱት አወዳሾች ብቻ ከሆኑ የዉድቀት ጎዳናን ተያይዟል ማለት ነው።በሂደትም ዉዳሴ መስማትን እየለመዳችሁ እውነቱን ለመስማትና ለመጋፈጥ ወኔ እያነሳችሁ ትሄዳላችሁ። በሂደትም ከተጨባጩ እውነታ ይልቅ የተዋበላችሁን ሀሰት መስማት ያስደስታችኋል። ያን ጊዜ ራሳችሁ ወድቃችሁ ሕዝቡንም ለዉድቀት ትዳርጋላችሁ።
ወደዳችሁም ጠላችሁ በቅርቡ ትረሳላችሁ!
🏀🏀🏀🏀🏀🏀🏀🏀🏀🏀🏀
ጥበቃና ፕሮቶኮል ቢያስፍልግም ከመጠን ያለፈ አጀባ ግን ልዩና ከሁሉ የላኩኝ ነኝ የሚል ስሜትን በዉስጣችሁ ስለሚፈጥር ቀንሱ።መታጀብንና መከበብ ሲበዛ አደገኛ ሱስ ይሆናል። መታጀብና መከበብ ከደም ስሩ የተዋሃደው ሰው እንኳንስ በእውኑ ገና አጀባውና ከበባው ሲቀርብት ቀርቶ ገና በምናቡ ሲያስብ ይዘገንነዋል። እንደ ተርታ ሰው ብቻውን ከሕዝቡ እንደ አንዱ ሆኖ መኖር ያስፈራዋል። ስለሆነም በሕጋዊም በሕገወጥም መንገድ በስልጣኑ ላይ መቆየት ግቡ ይሆናል። በመሆኑም የማያስደስተውን ምክር የሰጡ ሁሉ ፍላጎታቸው ስልጣኑን ሊነጥቁት መስሎ ይታየዋል። እርሱን የማውረድ መብት ያለው ሕዝቡ ጨምሮ በስልጣኑ የመጡበት ሁሉ ጠላቶቹ፥ የተቹት ሁሉ ባላንጣዎቹ ይሆናሉ። ስለሆነም አጉል ክብር ፍለጋ፥ ለታይታና አጀባ ቦታ አትስጡ።
እጅግ ይከበሩና ይታጀቡ የነበሩ በርካቶች ሲሞቱ ወዲያው እንደሚረሱ በኛ እድሜ እንኳን ብዙዎችን አይተናል። ይህን ጉዳይ ቆም ብላችሁ በሚገባ አስተውሉ።
አወድሶ አዳሪዎች እንኳንስ በሕይወት ሳትኖሩ ቀርቶ በእጃችሁ ያለው ስልጣንና ገንዘብ ሲጠፋ እነርሱን የምታገኙት ተረኛው ባለስልጣንና ባለሀብት ስር ሲያደገድጉ ነው። መከበርና መታወሰን ከፈለጋችሁ የሚያስከብራችሁንና የማያስረሳችሁን መልካም ተግባርን በስልጣን ዘመናችሁ ማሳካት ላይ ትጉ!
ተቀመጡ!
🚫🚫🚫
መሪነት ጊዜና ትኩረት መስጠትን ይጠይቃል። ትኩረታችሁ ሥራችሁ ላይ ይሆን ዘንድ የሀገር ዉስጥም ሆነ ዉጭ ጉዞ በመቀነስ ሥራችሁ ላይ አተኩሩ። በተቀበላችሁን ኃላፊነት ለመወጣት በቢሮ ሆናችሁ ሥሩ፤ አሰሩ። የሚሰሩትና የማይሰሩትን ተቆጣጠሩ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ከዓለም አቀፍ አቻ ተቋማት ጋር ግንኙት ማድረጉና በዓለም አደባባይ ሙስሊሞችን በተገቢው መልኩ መወከል አስፈላጊ ነው። ሆኖም በተጠሩበት ሁሉ መገኘት፥ በግብዣዎች ሁሉ ፕሬዝዳንቱ መገኘት አግባብ አይደለም። እንደየጉዳዩ ጠቃሚነት፥
ወቅታዊነትና አጀንዳነት የምንገኝባቸውንና የማንገኝባቸውን መደረኮችን መምረጥ እንዲሁም በመድረኩ በማን እንወከል የሚመለውን መለየት ተገቢ ነው።
እንደጥሪው ሁኔታ የምንገኝበትና የማንገኝበት፥ ለመገኘት ስንወስንም ፕሬዝዳንቱ፥ ምክትሎቻቸው፥ ጸሐፊው፥ ሥራ እኪያጁ አልያም የአንድ ዘርፍ ዳይሬክተር ሊወክለን ይችላል።
ጉዳዩ ከዒልምና ዑለማ ጋር የሚገናኝ ከሆነም መጅሊስን መወከል ያለባቸው የዑለማ ምክር ቤት አመራር አልያም አባላት ናቸው። በተጠራበት ቦታ ሁሉ የሚገኝ የመጨረሻው ከፍተኛው መሪ ራሱንም ሆነ የወከላቸውን አካላትን የማያከብር ነው። ለሕዘቡ ሲባል አቻውንና ደረጃውን ማወቅ ተገቢ ነው። በተጠራበት ሁሉ ራሱ ብቻ የሚገኝ መሪ የራሱን ደረጃና ክብር ይቀንሳል። መገኘት የሚኖርበት ከእርሱ ተቋምና ከርሱ ደረጃ ጋር አቻ የሆኑት አካላት በሚገኙበት መድረክ ብቻ ነው። እርሱም ቢሆን ገንብ፥ ጊዜና እውቀት መሰዋት የሚገባው ጥቅም ያለው ከሆነ ብቻ ነው። ያለዚያ እየዞርን የሌሎችን ድግሶች ስናሞቅ የኛው ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው ባለቤት አጥቶ መና ይቀርብናል።
አሳታፊ ተቋም ፍጠሩ!
✅✅✅✅✅✅
የመጅሊስ መሪዎች ስኬታማ መሆንና በታሪክ የሚጠቀስ ቁም ነገር መሥራት ከፈለጉ እንደ አባት ያለአመለካከት ልዩነት ፥ ያለጾታ አድሎና ያለ ብሄር ልዩነት ከ60 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሙስሊም ኢትዮጵያውንን ከጀርባው በማሳተፍ ከፊት ሆነው ለመምራት መጣር ይገባቸዋል።ይህ ማለት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፥ ወጣቶችም ሆኑ አዛውንቶች፥ ህጻናትና ታዳጊዎች የኛ ተቋም ነው ብለው ከጎኑ ሊቆሙ ሲችሉ ብቻ ሳይሆን በሚችሉት ሁሉ ከርሱ ጎን ቆመው ለዲናቸው መስራት ሲችሉ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቹ ሁሉም ወገን በተገቢው መልኩ ተወክያለሁ ብለው እንዲያምኑ ማድረግ ሲችል ነው። ይህ ይሆን ዘንድ መጅሊስን ሁሉም በርሱ ጥላና ከለላ ስር ሆነው ለስም ብቻ ሳይሆን በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት እድል ሊመቻችላቸው ይገባል።
በሁሉም እርከን በመጅሊስ የተመረጣችሁ በሙሉ! ሸሪዓው በሚፈቅደው መሰረት የሁሉንም ሙስሊሞችን አሳታፊነትና ጥቅም ለማስጠበቅና ለመጠበቅ ቁሙ። የሁሉም ሙስሊሞች ነን የሚለው ገለጻ በተግባር የሚረጋገጠው በአሳታፊነትና የሌሎችን መብትና ነጻነት በማክበርና በማስከበር ጭምር ነውና።
የጀመዓ አስተሳሰብ ይዞ ወደ መጅሊስ የሚመጣ ሰው በግልጽ ለራሱ መመለስ ያለበት ጥያቄ እንደጀመዓ እያሰባችሁ ያላችሁት «የኛ» የምትሉትን አስተሳሰብ መብት ለማስከበር ነው ወይንስ የኔ እገሌ የሚባሉትን ጀመዓ መብት እንዳይከበር ነው? በዚህ ጉዳይ ግልጽ እይታ እስካልያዛችሁ ድረስ ሁሉንም እኩል ማስተናገድና ማሳተፍ ከባድ ይሆንባችኋል።
በሥርዓትና መመሪያ የሚመራ ተቋም ፍጠሩ!
📮📮📮📮📮📮📮📮📮📮📮📮📮
በተቋማዊ አሰራርና ስኬት ላይ አተኩሩ እንጂ መጅሊስን በናንተ ስብዕና ዙሪያ የሚሽከረከርና የታጠረ አታድርጉት። መጅሊስን ከናንተ ስብዕና እስረኝነት አላቁትና በራሱ የሚቆም ተቋም አድርጉት። የተቋሙን ጥቅምና አካሄድ ለናንተ ጊዜያዊ አድናቆት ሳትሰዉት ተቋሙን ዘላቂ፥ ቅቡልነት ያለውና ጠንካራ በማድረግ ላይ አተኩሩ።ሁሉን ነገር እኔ ካላወቅኩትና ካላጸደቁት መፈጸም የለበትም ከሚል ተቋምን በሕግና አሰራር የሚመራ ሳይሆን የእናንተ እስረኛ ከማድረግ ነጻ አውጡት። ሠራተኞች መሥራት ያለባቸው በስልጣን ወሰናቸው ሕጉን፥ ደንቡንና እቅዱ ላይ ተመርኩዘው እንጂ የናንተን ይሁንታ. ባገኙና ባላገኙ ጉዳዮች ላይ ተመርኩዘው መሆን የለበትም።
ከናንተ የሚጠበቀው ሠራተኛው የናንተን ፊት፥ ስሜትን መሞቅና መብረድን ተከትሎ የሚሠራበት ሳይሆን ሁሉም ሕግን መከተል፥ መመሪያዎችን በማክበር፥ ማኑዋሎችንና ፖሊሲዎችን በመከተል የራስን ድርሻ በአግባቡ የሚወጣበት ምቹ ሁኔታ ያለበት ተቋምን መፍጠር ነው። ተቋሙ ያለናንተ የማይሠራ ካደረጋችሁት የተቋሙን እንቅስቃሴና እድገትን በናንተ ሁኔታ ላይ ጥገኛ በማድረግ ለውድቀት ትዳርጉታላችሁ።
እውነተኛ መሪዎች ሰዎች የነርሱን አርኣያነት ተከትለው የሚሠሩና በወሰናቸው ዉስጥ በራሳቸው መወሰን እንዲችሉ ማብቃት እንጂ በሁሉም ነገር የነርሱ ይሁንታ የሚጠበቅበት የተቋሙና የእንቅስቃሴዎች ሁሉ አሣሪዎችና ማነቆዎች አይደሉም። የመሪዎች ሚናው በተቋሙ የተዘረጉት እያንዳንዱ ስርዓት ያለእንቅፋት በአግባቡ መሥራታቸውን ማረጋገጥ እንጂ ያለነርሱ ስርዓቶች ሁሉ የማይሰሩ ቋጠሮዎች በመሆን አይደለም። በሁሉም እርከን በመጅሊስ ኃላፊነት ላይ ላላችሁ ሁሉ መልካም የሥራ ጊዜን እየተመኘሁ ለዛሬ በዚሁ አበቃሁ!
Click here to claim your Sponsored Listing.