Orthodox Media
Dhugaan Dhugaadha sobaan hin madaalamu. Namni Afaan dhaloota isaatin haa baratuun Galma keenya, Sirna uumamaan hunda jabeeffanna.
Har'as Arsii Bahaatti Manguddoo dabalatee Amantoonni ajjeefamanii jiru!
28/03/2026
የቤተ ክርስቲያኔ የቤት ሥራ፦ እኔነትን ለምእመናን እረፍት መገበር!
ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያኔ በምስልም በሐሳብም በኅሊናዬ ሲመላለስብኝ፤ መጀመሪያ የሚታየኝ ሌሎች ያልሠሩት ሥራ ሳይሆን እኔ ያጓደልሁት ትጋት፣ ሌሎች ያልተወጡት ኃላፊነት ሳይሆን እኔ የዘነጋሁት ድርሻ ብቻ ነው። ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስፋፋትና ስለ ወንጌል ተደራሽነት ሳስብ፣ ራሴን የምጠይቀው ጥያቄ "እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ?" የሚል ብቻ ነው። የትኛውን ቀዳዳ ለመድፈን እቆማለሁ? የትኛውንስ ጋን ለመደገፍ እንደ ጠጠር እሆናለሁ? በሚል ሐሳብ ራሴን እመረምራለሁ እንጂ፣ ለስሜቴና ለፍላጎቴ ፈጽሞ ፊት አልሰጥም። "እኔ ምን አድርጌያለሁ? ምን ያህልስ ገንዘቤን፣ እውቀቴን፣ ጊዜዬንና ጉልበቴን ለቤተ ክርስቲያን ክሳር አድርጌ አቅርቤያለሁ?" የሚለው ጥያቄ የዘወትር መዝሙሬ ነው።
በተለይም ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኔ ሸክም እንዳላበዛባት እጠነቀቃለሁ፤ ይልቁንም ሸክሟን ለማቅለል አቅጄ እሠራለሁ። ይህም የሚጀምረው ከራሴ ነው። ቤተ ክርስቲያን እኔን ለማስተማርና ለማነጽ ጊዜዋን፣ ገንዘቧንና እውቀቷን እንዳታወጣ፤ ቢያንስ የራሴን የቤት ሥራ እኔው እወስድላታለሁ። እኔን ለማስተማር እንዳትደክም የትምህርት ወጪዬን ራሴ እየሸፈንኩ፣ ጊዜ መድቤና በመደበኛ መርሐ ግብር ታቅፌ በከፍተኛ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ትምህርቷን እየተከታተልኩ እገኛለሁ። መጻሕፍትን መግዛት እንደ ትልቅ ሥራ ቆጥሬ፣ ወጪው እንዳይከብደኝ በመጽሐፍ ዕቁብ እየተሳተፍኩ፣ አጥንቼና ማስታወሻ ይዤ ለነገ አገልግሎት የሚሆን ዝግጅት አደርጋለሁ። ዕውቀቴ ለሚፈልጉት ሁሉ ያለ ስስትና ያለ ገደብ ለማካፈልም ዘወትር ዝግጁ ነኝ።
ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ በቤቴም ውስጥ ይቀጥላል፤ ባለቤቴ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን እንድትማር አበረታታታለሁ፣ ልጆቼም የቤተ ክርስቲያን ፍቅርና ሥርዓት በውስጣቸው እንዲታተም ከባለቤቴ ጋር በመሆን በትጋት እንሠራለን። ዓላማዬ አንድ ነው፦ ቤተ ክርስቲያን እኔን ፍለጋ እንዳትደክም፣ እኔን ለማስተማር ወጪ እንዳታወጣ ራሴን መቻል! ለእኔ ልታውለው የምትችለውን ድካምና ወጪ ለሌላ ለአንዲት ነፍስ ማዳኛ እንድትጠቀምበት በማሰብ ራሴን ለሥራዋ አዘጋጃለሁ። እያንዳንዳችን በራሳችን ወጪ ራሳችንን ብናስተምር፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ሸክም መሆናችን ቀርቶ ለሌሎች የምንተርፍ ብርቱ የቤተ መቅደስ ምሶሶዎች እንሆን ነበር።
Click here to claim your Sponsored Listing.