Daamileen Lafa

Daamileen Lafa

Share

Lubbuun jiraachuun mirga Uumamaat.Ilma Namaa kamiiyyuu mirgi jiraachuu kabajamuu qaba.

30/05/2025

ኦሮሙማ ምን ማለት ነው?
----
አፈንዲ ሙተቂ
---
እስቲ ከቀላል ነገር እንነሳ። ተከታዮቹን የአፋን ኦሮሞ ቃላት ከአማርኛ ፍቺዎቻቸው ጋር ይመልከቷቸው።

አንድ= tokko

አንድነት= tokkummaa

ዱርዬ። kashlabbee

ዱርዬነት= kashlabummaa

ማን= Eenyu

ማንነት= Eenyummaa

ነፃ= Bilisa

ነፃነት= Bilisummaa

አስመሳይ= Fakkeessituu

አስመሳይነት= Fakkeesitummaa

ኢትዮጵያ= Itoophiyaa

ኢትዮጵያዊነት= Itoophiyummaa

ኦሮሞ = Oromoo

ኦሮሞነት= Oromummaa

ወዘተ...
------
ከላይ በቀረቡት ምሳሌዎች መሠረት "ኦሮሞ" (Oromoo) በሚለው ስም ላይ "ነት" ("mmaa") የሚል ቅጥያ ሲጨመርበት "ኦሮሞነት" ወይንም "Oromummaa" የሚል አዲስ ስም ይፈጠራል ማለት ነው።

እኛ አፍ መፍቻችን Afaan Oromoo (ኦሮምኛ) የሆነን ሰዎች የምናውቀው እውነታ ይህ ነው። በዘመናችን ቃሉን ከተገቢው ፍቺው አውጥተውት "ኦሮሙማ" የሚባል ርዕዮተ ዓለም እና አዲስ የጽንፈኝነት መንገድ እንደተፈጠረ የሚናገሩ እና የሚጽፉ ግለሰቦች እና ቡድኖች የስነ-ልሳን እና የታሪክ ማስረጃ የላቸውም። አራት ነጥብ!!
------
"ኦሮሙማ" በዶክተር ዐቢይ ዘመን፣ ወይንም በOLF ዘመን የተፈጠረ ቃልና ርእዮት አይደለም። ኦሮሞ የሚባል ሕዝብ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ነው። ወደፊትም ሕዝቡ እስካለ ድረስ ኦሮሙማ ይኖራል።
-----
አዎን! "ኦሮሙማ" ሲባል "ኦሮሞነት" ማለት ነው። ይህም የኦሮሞ ሕዝብ የማንነት መለያ የሆኑትን ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ታሪኩን፣ ስርዓቱን፣ ኪነ-ጥበቡን፣ ስነ-ቃሉን፣ ትውፊቱን፣ ልማዱንና ሌሎችንም መውደድ፣ ማንጸባረቅና ማስተማር፣ እንደዚሁም ለህዝቡ የኑሮና የስነ-ምግባር ደንቦች ተገዝቶ መኖር ማለት ነው።
------
እኔ አፈንዲ ለረጅም ዓመታት በጋዜጣ፣ በመጽሔቶች፣ በብሎግ እና በፌስቡክ ገጾቼ ላይ ስለኦሮሞ ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ቋንቋ፣ ስነ-ቃል፣ ኪነ-ጥበብ ወዘተ ስጽፍ ነበር። "ቦረና እና በሬንቱ" በተሰኘው መጽሐፌ ደግሞ እነዚህን የህዝቡን የማንነት ምልክቶች በስፋት አጥንቼ ለተደራሲው በዝርዝር ጽፌአለሁ። ኦሮሙማ ማለት ይኸው ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም። ኖሮትም አያውቅም።

አንዳንዶች "ኦሮሙማን የፈጠረው ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ ነው" ይላሉ። ይገርማል! ግለሰብ የአንድን ትልቅ ብሄር መገለጫ ሊፈጥር ይችላል እንዴ? አሰፋ ጃለታ ስለኦሮሙማ ነው የጻፈው። እርሱ ያለበትን የፖለቲካ ዑደት ተንተርሶ ኦሮሞነትን በራሱ መንገድ ሊገልጽ ይችላል። ነገር ግን ኦሮሙማን አልፈጠረም። መፍጠርም አይችልም።
-------
ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገራችን በሰፈነው አገዛዝ ሳቢያ ብዙ ነገሮች ተበጥብጠዋል። ሀገሪቷም ከባድ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። ሀገሪቱን በሚገዙት ወገኖችና በተቃዋሚዎቻቸው መካከል ያለው ልዩነት ተካርሯል።

ከዘመናችን ገዥዎች መካከል አውራ የሚባሉት ከኦሮሞ ሕዝብ የወጡ መሆናቸው ይታወቃል። እነዚህ አውራዎች በፌዴራል እና በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ብዙ ሕዝብ ያስቀየሙ እርምጃዎችን ወስደዋል።

ታዲያ አንዳንዶች አገዛዙን ነጥለው ማውገዝን ትተው "የኦሮሙማ መንግሥት እንዲህ አደረገ" የሚል አነጋገር ይደጋግማሉ። ነገር ግን የኦሮሙማ መንግሥት የሚባል ነገር የለም። የአቢይ መንግሥት "የምከተለው ርዕዮት ኦሮሙማ ነው" ብሎ አስታውቋል እንዴ? እንደዚህ ካለ "ውሸታም ነህ" እንለው ነበር። ነገር መንግሥቱ ይህንን ብሎ አያውቅም። እንደዚህ ቢል ደግሞ ትልቅ fallacy ሰርቷል ማለት ነው። ምክንያቱም ኦሮሙማ ማለት እያንዳንዱን ኦሮሞ የሚያስተሳስር የማንነት መግለጫ እሴት ከመሆኑ ውጪ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወይንም ፍልስፍና አይደለም።
------
በመጨረሻ

ስድሳ ሚሊዮን የሚሆነው የኦሮሞ የሚያውቀው የኦሮሙማ ፍቺ እና ትርጉም እኔ የጻፍኩት ነው። ኦሮሞዎች ከደም በላይ በኦሮሙማ ነው የተሳሰሩት። ኦሮሙማ የሕዝቡ መገለጫ ነው። እርሱን እንደ negative ማየት ትልቅ ስሕተት ነው።

በስመ ተቃዋሚነት የኦሮሞን ሕዝብ ከዶክተር አቢይ ግሩፕ ጋር እየጨፈላለቁ መግለጽን የለመዱት እነ እስክንድር ነጋ እና Ethio-360 የተሰኘው የሚዲያ ተንታኝ ተብዬዎች ኦሮሙማን የሚገልጹበትን ሁኔታ ሕዝቡ አያውቀውም። እነኝህ ሰዎች የኦሮሞ ቋንቋንም ሆነ ባህልን አያውቁትም። በመሆኑም በየትኛውም መንገድ የኦሮሙማ ኤክስፐርት መሆን አይችሉም። "የኦሮሙማ መንግሥት" የሚባል ነገር የለም። "ኦሮሙማ" የሚባል ልዩ የፖለቲካ ርእዮትም የለም። ቴዎድሮስ ጸጋዬ እና ዘመድኩን በቀለ የሚሰብኩት የኦሮሙማ ትንታኔ ከእነርሱ የጥላቻ አዕምሮ የመነጨ እንጂ ደጋፊ መሠረት ያለው አይደለም።
-----
ስለኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላም፣ ወንድማማችነት፣ የጋራ ዕድገት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ወዘተ የሚያስብ ሰው ኦሮሙማን በትክክለኛው መንገድ መረዳት አለበት። "ለለውጥና ለነፃነት እታገላለሁ" የሚሉ ኃይሎችም ፖለቲከኞችንና ባለስልጣኖችን ሳይሆን የኦሮሞን ሕዝብ የልብ ትርታ ማድመጥ አለባቸው። እውነቱ ያለው ሕዝቡ ዘንድ ነው።

እዚህ የለጥፍኩት የኦሮሙማ ገለጻ በእያንዳንዱ ኦሮሞ የሚታወቅና ሕዝቡ የሚያምንበት ነው። 60 ሚሊዮን ኦሮሞዎች በፖለቲካ አመለካከት ቢለያዩም በኦሮሙማ ላይ ልዩነት የላቸውም። እኛ ኦሮሞዎች ይህንን ስንል ኦሮሞ ያልሆኑት ሐቁን መቀበል ይኖርባቸዋል። እስከ አሁን እንዳየሁት ግን በሶሻል ሚዲያ ላይ "ውር ውር" የሚለው troll ለሐቅ ቦታ አይሰጥም። እኛ የምንለውን እውነታ ይረግጥና ለራሱ መስማት የሚፈልገውን ትንታኔ በሌሎችም ላይ ሊጭን ይታገላል። እንዲህ ዓይነቱ ባህል ካልተስተካከለ መግባባት አይቻልም። በተለይም አንድን ሕዝብ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ ስለራሱ የሚናገረውን በቅን ልቦና ካልወሰዱት ትርፉ "እምቦጭ ዘጭ" መሆን ብቻ ነው። ይህ አካሄድ ሊታረም ይገባል።
-------
ድል ለሰፊው ሕዝብ
-------
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 18/2017
-----
=> የቴሌግራም ቻነሌ የሚከተለው ነው
(Here is my Telegram Channel)

https://t.me/afandishaHarar

Want your public figure to be the top-listed Public Figure in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Category

Address

Addis Ababa