OLA POST

OLA POST

Share

WBOn duratti!

28/12/2025

የእድሩ ስም ጠሪ
-----
ከተስፋዬ ገብረአብ
----
እለቱ ሰንበት ነው:: ደብረዘይት። የቢሾፍቱ ቀበሌ የሃዲድ በላይ እድርተኞች ለቀብር ቃጂማ ጊዮርጊስ ተሰብስበዋል። ሰንበት ስለሆነ ነው መሰል ቀብር ላይ በርከት ያለ ሸኚ ተገኝቶአል። በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኞች ልማድና ደንብ መሰረት በቀብር የተገኘና ያልተገኘውን ለማጣራት የስም ጥሪ ይካሄድ ጀመር። ስም ጠሪው ባሻ መላኩ እርጅና ተጭኖአቸዋል። ቢሆንም ግን ድምፃቸው እንደ ባቡር ጡሩምባ ነው። በፀጥተኛው የመቃብር ስፍራ እየተምዘገዘገ ያለችግር ከአስከሬን ሸኚው ጆሮ ይደርሳል፣
“ወይዘሮ ፈትለወርቅ ሞላ”
“አቤት!”
“አስር አለቃ እርገጤ ሺባባው”
“አለሁ!”
“ወይዘሮ ከበቡሽ ደሜ”
“አቤት!”
“አቶ ዳኜ ተማም”
ምላሽ አልነበረም፣
“አቶ ዳኜ!?” አሉ ስም ጠሪው በድጋሚ፣
“አለሁ! አለሁ! “ የሚል ድምፅ ተሰማ፣
ይህን ጊዜ ሽማግሌው ስም ጠሪ እብድ የሚያህለውን ዶሴ አጥፈው እርሳሳቸውን ጆሮአቸው ላይ ሰክተው ከፊታቸው ለተኮለኮሉት የእድሩ አባላት ማስጠንቀቂያ ይሰጡ ጀመር፣
“ስሙኝ ቀባሪዎች! እኔ ላንቃዬ እስቲዘጋ የምጮኸው እንደ ፊልፕስ ሬድዮ ባትሪ ውጬ አይምሰላችሁ። በዚህ እድር በቀን አንድ ሰው ይሞታል። በየቀኑ እጮሀለሁ! በ75 ብር ስጮህ መዋሌ ወገኖቼን ልጠቅም ካልሆነ ገንዘቧ ምን አላት? ስለዚህ ካንድ ጊዜ በላይ አልጠራም! ቀሪ ተባልሁ ተብሎ ቅያሜ እንዲመጣብኝ አልፈልግም። ተቀጣሁ ተብሎ ወቀሳ እንዲወርድብኝ አልፈቅድም። ጆሮአችሁን ተክላችሁ ስማችሁን አዳምጡ። እኔ የቁራ ዘር የለብኝም። በየሜዳው የሚጮህ ቁራ ነው። በየባህር ዛፉ፣ በየገደሉ፣ በዋርካ ላይ ተጎልቶ ሲጮህ የሚውል ቁራ ነው፣ እኔ ግን ቁራ አይደለሁም”
ስም ጠሪው በተጨማደደች መሃረም ግንባራቸው ላይ ያቸፈቸፈውን ላብ አደራረቁና ጥሪውን ቀጠሉ፣
“ወይዘሮ የሁዋላሸት አለሙ”
“አለሁ!” አለ የወጣት ወንድ ድምፅ፣
“ደሞ አንተ ማነህ?”
‘ልጃቸው ነኝ!”
ጥሪው ቀጠለ፣
“አቶ ከበደ ማሞ”
ምላሽ የለም፣ ቀሪ።
“ፊታውራሪ የሽዋሉል ግርማቸው”
ምላሽ የለም፣ ቀሪ።
“እመት ጌጤ እሸቴ”
“ታመዋል!” የሚል ድምፅ ተሰማ።
“አቶ ተሰማ ታደለ”
ምላሽ የለም፣ ቀሪ። የእድሩ ስም ጠሪ ግምባራቸውን በመሃረም እያበሱ ቀና አሉ፣
“ስሙኝ ቀባሪዎች! ቀሪ በዝቶአል። እንዴት ነው ነገሩ? አዲስ ድንኩዋን ገዝተን የምረቃ ግብዣ የተባለ ለታ ግን እድርተኛው ግልብጥ ብሎ ነበር የመጣው። ትርፍ ሰው ሁሉ ነበር። የቀበርናቸው ሰው ወክለው ነው? ቀብር ሲባል ግን ቀሪ ይበዛል? ነግ በኔ ነው። ዛሬ ያላቃበርነው ነገ አይቀብረንም…”
ምክርና ተግሳፁን እንዳበቁ ጥሪውን ቀጠሉ፣
“አቶ ሃይለራጉኤል ተካ”
“አቤት”
“ወይዘሮ ኪሮስ ገብራይ”
“አለሁ!”
“ወይዘሮ አረጋሽ አባተ”
ምላሽ የለም፣ ቀሪ።
“አቶ ኩራባቸው ታዬ”
“አቤት!”
“መምህር ገረመው ደበላ”
“አቤት!”
“ወይዘሮ የወርቅውሃ ታደሰ!”
ምላሽ የለም። የእድሩ ስም ጠሪ በድጋሚ “ወይዘሮ የወርቅ ውሃ! ‘ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጠሩ። መልስ የለም። ሽማግሌው እንዲህ ሲሉ ተናገሩ።

"እኝህ ሴትዮን ምን አግኝቷቸው ነው? በጣም ደግ ሰው ናቸው። ቀብር ቀርተው አያውቁም። ወይዘሮ የወርቅውሃ!"

በዚህ ጊዜ አጠገባቸው ቆሞ የነበረ አንድ ጎልማሳ ወደ ጆሮአቸው ጠጋ ብሎ አንሾካሾከ።

“ይዝለሉት ባሻ፣ ዛሬ የቀበርነው ወይዘሮ የወርቅውሃን ነው”
-----
(ልቦለድ፣ 1989 አዲስ አበባ - ተስፋዬ ገብረአብ)

Want your public figure to be the top-listed Public Figure in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Category

Website

Address

Addis Ababa