WMCC

WMCC

Share

AddisWalta - AW
አዲስ ዋልታ
Walta Media and Communication Corporate Who We Are
Walta Media and Communication Corporate S.C.

09/06/2026

የፖሊሲ ጉዳይ ቅኝት - ሰኔ 2፣ 2018 ዓ.ም

08/06/2026

ሀገራዊ ምክክር እና ሀገር በቀል የእርቅ ዕሴቶች...

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንዲሁም ታሪካዊና መዋቅራዊ ቅሬታዎችን በውይይት ለመፍታት ታላቅ የብሔራዊ ምክክር ሂደት እያካሄደች ትገኛለች።

የዚህ ጉዞ ስኬት የሚወሰነው ከውጭ በሚቀዱ የፖለቲካ ቀመሮች ሳይሆን ማህበረሰቡ ለዘመናት ጠብቆ ባቆያቸውና ከማንነቱ ጋር በተሳሰሩ የሰላምና የዕርቅ ዕሴቶች ላይ መመስረት ሲችል ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔረሰቦች የሚኖሩባት የባህልና የማንነት ሕብረቀለም እንደመሆኗ መጠን እያንዳንዱ ማህበረሰብ ግጭቶችን የሚፈታበት፣ ፍትህን የሚያሰፍንበት እና የተናጋ ማህበራዊ ትስስርን የሚያድስበት የራሱ የሆነ ሀገር በቀል የዕርቅ ሥርዓት አለው።

ከእነዚህ ውድና ሕያው ማህበራዊ ዕሴቶች መካከል በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የደራሼ ብሔረሰብ ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት “ደሃ” ተጠቃሽ ነው።

በደራሼ ማህበረሰብ ዘንድ “ደሃ” ወይም ሽምግልና ማለት እንዲሁ ግጭት ሲከሰት ብቻ የሚደረግ የጊዜያዊ ስምምነት ሂደት አይደለም። ይልቁንም ፍትህ የሚረጋገጥበት፣ የበደለ የሚጠየቅበት፣ የተበደለ የሚካስበትና ጠቅላላው ማህበራዊ ኑሮ ሕጋዊና ሞራላዊ እውቅና የሚያገኝበት ጠንካራ ዕሴት ነው።

ይህንን ሥርዓትን የሚመሩትና የሚያስፈጽሙት መሪዎች “ካዳያ” በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ መሪዎች የሚመረጡት በማህበረሰቡ ሕገ-ህሊና ውስጥ ባሉ ጥብቅ መስፈርቶች ሲሆን÷ የካዳያዎች የሥልጣን ዘመን ሁለት ዓመት ብቻ ነው።

ይህ የሚያሳየው በባህላዊ ሥርዓት ውስጥ የሥልጣን ሽግግርና ለሌሎች ዕድል የመስጠት የዴሞክራሲ መርህ ቀድሞውኑ የነበረ መሆኑ ነው።

የደራሼ የዕርቅና የፍርድ ተግባር የሚከናወነው የማህበረሰቡ መረጃ የሚለዋወጥበት፣ ወጣቶችና አዛውንቶች የሚገናኙበት ዋነኛ ማዕከል በሆነው “ሞራ” በሚባል ጥላ በሚሰጡ ታላላቅ ዛፎች ሥር ድንጋዮች እንደ እርከን ከፍ ተደርገው በተዘጋጁ የሸንጎ ስፍራዎች ላይ ነው።

በደራሼ ባህል ሞራ ላይ ተከስሶ መቆም ትልቅ ማህበራዊ ውርደት ተደርጎ ይቆጠራል። ይህ ማህበራዊ ሞራል ሰዎች ወንጀልና ጥፋት ከመስራታቸው በፊት ራሳቸውን እንዲገቱ ያደርጋቸዋል።

የደሃ የዳኝነት ሂደት ፍፁም ሰላማዊና ሥርዓታዊ ሲሆን÷ ተበዳዩ አቤቱታውን ካቀረበ በኋላ ተከሳሹ በምስክሮች ፊት እንዲቀርብ ይጠራል። ተከሳሹ የቀረበውን ጥሪ አሻፈረኝ ካለ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ማህበረሰባዊ ማዕቀብ ይጣልበታል።

በዳዩ በጥፋቱ ካመነ ደግሞ ሌላው አስደናቂ እሴት ይታያል፤ የካሳውን ክፍያ ጥፋተኛው ግለሰብ ብቻውን ሳይሆን የጎሳው አባል በሙሉ አዋጥቶ እንዲከፈል ይደረጋል።

ይህ እኔነትን ወደ እኛነት የሚቀይርና የአንዱ ጥፋት የሁሉንም ትኩረት እንዲስብ የሚያደርግ የጋራ ኃላፊነት መገለጫ ሲሆን÷ ዕርቁ የሚደመደመው ፍፁም ማህበራዊ ትስስርን በሚያድስ ታላቅ በዓል ነው።

ለዕርቁ ማሳረጊያ የሚሆን “ጨቃ” የተባለው ባህላዊ መጠጥና ምግብ የሚዘጋጀው የጎሳ አባላት እህል አዋጥተው በጋራ በመሥራት ነው።

በዕርቁ ቀን ከተበዳይና ከበዳይ ወገን የመጣው ምግብና መጠጥ አንድ ላይ ተደባልቆ በአንድ ማዕድ ይበላል። ፅዋቸውን ካነሱበት ሰዓት ጀምሮ ቁርሾው ሙሉ በሙሉ ተረስቶ ቀኑን በደስታ ያሳልፋሉ።

የደራሼ “ደሃ” ሥርዓት አሁን ኢትዮጵያ ለጀመረችው ብሔራዊ የምክክር ሂደት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ስልቶችንና ፍልስፍናዎችን ማበርከት ይችላል።

የዘመናዊው የፍትህ ሥርዓት ጥፋተኛውን መቅጣት ላይ ብቻ ሲያተኩር÷ የደሃ ሥርዓት ግን ትኩረቱ የተበላሸውን ግንኙነት ማደስ ላይ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩም እንደ ደራሼ ዕርቅ ሥርዓት ይቅርታንና ማህበራዊ ፈውስን ማምጣት ላይ ሊያተኩር ይገባል።

ዘመናዊነት ማለት የራስን መልካም እሴት መጣል ሳይሆን ባለው ሀገር በቀል እውቀት ላይ ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ እሴት መጨመር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ሆነ መላው ሕዝብ እነዚህን ሕያው የሆኑ የባሕል ዕሴቶችን ለሀገራዊ መግባባት ሊጠቀምባቸው ይገባል።

የደራሼ ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት የሚያስተምረን ታላቅ እውነት ቢኖር ችግሮቻችንን እኛው ራሳችን በራሳችን መድረክ በጥበብና በፍቅር መፍታት እንችላለን የሚለውን ዘላለማዊ ሀቅ ነው።

Photos from WMCC's post 08/06/2026

በኮሪደር ልማት የተዋበችው ወልድያ ከተማ በምስል፡-

08/06/2026

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች እነማን ናቸው?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚገኙ እና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የአጀንዳ ሃሳቦችን ማሰባሰቡ የሚታወቅ ነው፡፡

በዚህ የምክክር ሂደት በክልል/ ከተማ አስተዳደር ደረጃ፣ በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በዲያስፖራው ማህበረሰብ ዘንድ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በኮሚሽኑ ተደራጅተው ለመጨረሻው የአጀንዳ ቀረፃ እየተዘጋጁ ነው፡፡

👉ለመሆኑ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ የሚመካከረው ማን ነው?

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ተሳትፎን የሚያደርጉ አካላት ኮሚሽኑ አጀንዳ ካሰባሰበባቸው ባለድርሻ አካላት የተመረጡ/ የተወከሉ ሲሆን ይህም በባለድርሻ አካላቱ እውቅና ሲከናወን ቆይቷል፡፡

በዚህ መሰረት በክልሎች/ ከተማ አስተዳደሮች፣ እና በዲያስፖራው ማህበረሰብ ዘንድ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ወቅት በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ እነሱን ወክለው የሚመካከሩ ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል በኩሚሽኑ አሰራር ስርዓት መሰረት በክልሎች/ከተማ አስተዳደሮች እና በፌዴራል ተቋማት በሚገኙና ወኪሎቻቸውን በአጀንዳ ማሰባሰብ ወቅት እንዲመርጡ ያልተደረጉ ባለድርሻ አካላት ወኪሎቻቸውን በደብዳቤ ወክለው ለኮሚሽኑ እንዲያሳውቁ ኮሚሽኑ ለባለድርሻ አካላቱ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ መሰረት በአጠቃላይ 4,000 የሚጠጉ ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት የሀገራዊ ምክክር ሂደት

👉የየወረዳው የሕብረተሰብ ክፍል ወኪሎችን

👉የክልል/ከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ወኪሎችን

👉የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ወኪሎችን እና

👉የዲያስፖራ ማህበረሰብ ወኪሎችን ያሳትፋል፡፡

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!

Want your business to be the top-listed Media Company in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Telephone

Address

Addis Ababa