ASER MEDIA
ASER MEDIA is a news and current affairs channel. follow us on Facebook, tiktok, and YouTube.
08/06/2026
313 ምርጫ ክልሎች እስካሁን ውጤት አላሳወቁም
-------
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ከተካሄደባቸው 1 ሺህ 138 የምርጫ ክልሎች ውስጥ እስካሁን ውጤት ይፋ ያደረጉት 8 መቶ 25ቱ ብቻ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ 3 መቶ 13 የምርጫ ክልሎች አሁንም በድምፅ ማዳመር ሂደት ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል። የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ዛሬ ከሰዓት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በርካታ የምርጫ ክልሎች ውጤቱን ይፋ ለማድረግ ወደኋላ መቅረታቸውን ገልጸው ለዚህም እንደ ሲዳማና አዲስ አበባ ያሉ አካባቢዎችን በምሳሌነት አንስተዋል። በሲዳማ ክልል ካሉ 19 የምርጫ ክልሎች ውስጥ እስካሁን ውጤት የተለጠፈው በሁለቱ ብቻ ሲሆን፣ ለዚህም በሀዋሳ ያሉ 303 የምርጫ ጣቢያዎች መብዛትና የዕጩዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን በማዳመር ሥራው ላይ መዘግየት መፍጠሩ ተብራርቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 33 የምርጫ ክልሎች ውስጥ 11ዱ ብቻ ውጤት ይፋ አድርገው ወደ ማዕከል የላኩ ሲሆን፣ የዋና ከተማው መዘግየትም ከሌሎች ክልሎች ጋር ተመሳሳይ በሆኑ ምክንያቶች የመነጨ መሆኑ ተጠቁሟል። በሌላ በኩል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉ 22 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ውጤት ይፋ ያደረጉት ሁለቱ ብቻ ሲሆኑ፣ ለዚህ መዘግየት ደግሞ የምርጫ ጣቢያዎቹ ከምርጫ ክልሉ ማዕከል ያላቸው ርቀት ከፍተኛ መሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
07/06/2026
በአርሲ ግጭት የኢሰመኮ ሪፖርት!...
-----
መንግሥት ተገቢውን ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እና ተጎጂዎችን ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል አለ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ግንቦት 23 እና 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ክትትል እና ምርመራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
ኢሰመኮ ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በአካባቢው በአካል በመገኘት ከዐይን እማኞች፣ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ባሰባሰባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው “በተለምዶ ኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን በፈጸመው ጥቃት የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላትና ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፣ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ የንብረት ውድመት እና ቃጠሎ መድረሱን ለማረጋገጥ ችሏል።
ኢሰመኮ በምርመራ ሂደቱ እንዳረጋገጠው በአሰኮ ወረዳ ደለተ ጫፋ ቀበሌ አካባቢ ከግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በመስተዋሉ የአካባቢው ሚሊሻዎችና የኦሮሚያ ጸረ ሽምቅ ውጊያ ፖሊስ አባላት በስፍራው በመሰማራታቸው “በተለምዶ ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና በተሰማሩ የጸጥታ አካላት መካከል ግጭት ተፈጥሯል። ግጭቱን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ላይ ታጣቂ ቡድኑ ባደረሰው ጥቃት ከአካባቢው መሸሽ ባልቻሉ ኃይሉ ንጉሴ እና ሰሙ አባይነህ በተባሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዲሁም በአካባቢው ከብቶች በመጠበቅ ላይ የነበረ ባቶ ሰፈኖ የተባለ የእስልምና እምነት ተከታይ በአጠቃላይ የሦስት ሲቪል ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ ችሏል።
በተጨማሪም ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ባልታወቁ ቤቶች ላይ ቃጠሎ መድረሱን፣ የጠለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መቃጠሉን፤ ቢዮ ቡጡሌ የሼክ ሙስተፋ መስጅድ አጥር ላይ ጉዳት መድረሱን፣ በድለተ ጫፋ ጤና ጣቢያ፣ በነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶችና የንግድ መደብሮች ላይ በመደዳ ዘረፋ መፈጸሙን እንዲሁም ከ2,650 በላይ የሚገመቱ የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ አረጋግጧል።
ኢሰመኮ በአርሲ ዞን በሽርካ፣ በአሰኮ፣ በአንቆሎ ዋቤ፣ ጉና እና መርቲ ወረዳዎች ላይ በታጣቂዎቹ ሲፈጸሙ የነበሩ ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ እና ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ በተለያዩ ጊዜያት ማሳሰቡ ይታወሳል። መንግሥት በአካባቢው ላይ በተደጋጋሚ መሰል ጥቃቶች እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መከሰት መቀጠላቸው አሳሳቢ መሆኑን ከግምት በማስገባት ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የጀመራቸውን ጥረቶች በማጠናከር በአስቸኳይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩ እና ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ነዋሪዎችን ወደ ተረጋጋ ሕይወት የመመለስ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመንግሥትና በሌሎች አጋር አካላት በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ የአስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ኢሰመኮ ያሳስባል። በሌላ በኩል ኢሰመኮ ጉዳዩን አስመልክቶ ዝርዝር የምርመራ ሪፖርት ይፋ የሚያደርግ መሆኑን እየገለጸ፤ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በአግባቡ ሳያረጋግጡ የሚሰነዘሩ ፍረጃዎችና ቅስቀሳዎች ተጨማሪ ግጭት እንዲፈጠር የማነሳሳት ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ ማናቸውም ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀርባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ኢሰመኮ በዜጎች ላይ ለደረሰው ሞትና ጉዳት ማዘኑን ገልጸው በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አሳሳቢ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አክለውም መንግሥት ሁኔታውን ለማረጋጋት እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ተግባራት መቀጠል ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በማንኛውም ጊዜ የጸጥታ ሥጋት ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ በቂ የጸጥታ ኃይሎች በመመደብና ተመሳሳይ ጥቃቶችን የመከላከል ሥራ በመሥራት የነዋሪዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት እና የንብረት መብቶች ለአደጋ እንዳይጋለጡ እንዲያደርግ፣ ተገቢውን ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እና ተጎጂዎችን ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ እንዲሁም ሁሉም አካላት የተፈጠሩ ችግሮችን ከማውገዝ ባሻገር ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ መግለጫዎች እና ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል።
05/06/2026
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
-------
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ማለዳ ላይ፤ የመጀመሪያው የወገግታ ጭላንጭል በከፍታማዎቹ የኢትዮጵያ ተራሮች ላይ ፈንጥቆ ጨለማውን ሳይቀድ በፊት ኢትዮጵያውያን ረጃጅም ሰልፍ ተሰልፈዋል። በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በባሕር ዳር እንዲሁም ስማቸው በዓለም አቀፍ የዜና ጋዜጣዎች ላይ ፈጽሞ ሊወጣ በማይችሉ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ያሉ ወንዶችና ሴቶች፤ ወሳኝ ተግባር ለመፈጸም በሰልፍ ቆሙ። ድምፅ ሰጡ! ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ከሃምሳ አራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተመዝግበው ነበር። ይህ ቁጥር ከአንዳንድ ሀገሮች አጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር በላይ ነው። ይህ ምርጫ እውነተኛ ስለመሆኑ ጥያቄ ለሚያነሣ ለማንኛውም አካል ግልጽ እና የማያሻማ ምላሽ ሰጥቷል!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ52,000 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ከ50,188 በላይ የሚሆኑት በሰዓቱ ተከፍተው ቀኑን ሙሉ መራጮችን ሲያስተናግዱ እንደነበር አረጋግጧል። ከ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ ከ10,438 በላይ ዕጩዎች እና 80 የግል እጩዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን ለማሸነፍ ተወዳድረዋል። ይህ በማንኛውም ሊለካ በሚችል መሥፈርት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ እና በውሳኔ አሰጣጥም ሆነ በአስተዳደራዊ ረገድ እጅግ በረቀቀ ሁኔታ ተግባራዊ የተደረገ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የታየበት ኩነት ነበር።
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ክቡር ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩትና ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ታዛቢዎችን ያቀፈው የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫውን “ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በሰፊው በሚደግፍ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተካሄደ” ሲል ገምግሞታል። በቀድሞዋ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ክብርት ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ የሚመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፥ በታዘቡባቸው ጣቢያዎች ሁሉ የምርጫ ሳጥኖች በትክክል የታሸጉ መሆናቸውን፣ የፓርቲ ወኪሎች በሂደቱ በሙሉ መገኘታቸውን እንዲሁም ምርጫው አስደናቂ ተቋማዊ፣ አስተዳደራዊና የቴክኖሎጂ ዕድገትን ያሳየ መሆኑን አረጋግጧል። የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ይሄንን ምርጫ «የበርካታ አዳዲስ ምዕራፎች ምርጫ» ሲል ሰይሞታል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድምፅ መስጠት ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተመለከተ አረጋግጧል። የሲቪክ ማኅበረሰብ ታዛቢዎች ጥምረት በምርጫ ቦርድ እውቅና ከተሰጣቸው 55 ድርጅቶች 65,299 የታዛቢዎችን በመላ ሀገሪቱ ያሠማራ ሲሆን፥ 99 በመቶ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያለምንም ዕንቅፋት የመታዘብ ዕድል ማግኘቱን አረጋግጧል። እነዚህ ተዓማኒነት ያላቸው ሀገራዊ እና አኅጉራዊ ተቋማት ያደረጓቸው ግምገማዎችና የሰጧቸው እውነተኛ ፍርዶች ናቸው። እነዚህ ለአፍሪካ ጥላቻ ካላቸው ወይም የአፍሪካን ዴሞክራሲ በውጫዊ መሥፈርቶች ከሚለኩ ተቋማት የተደመጡ ድምፆች አይደሉም።
አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተንታኞች ይሄንን ምርጫ እንደ ንግሥና በዓል አድርገው ያቆሸሹት ሲሆን ውጤቱም አስቀድሞ የተወሰነ ድራማ እንደነበር አድርገው ሊያቀርቡት ሞክረዋል። እነዚህን መግለጫዎች ከእውነታው ፈጽሞ የራቁ፣ በጥናትና ትንተና ላይ ያልተመሰረቱ እንዲሁም ነፃና የታሰበበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫቸውን በኩራት ላደረጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ክብር የማይሰጡ በመሆናቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ የማይቀበላቸው መሆኑን ያረጋግጣል። አስቀድሞ የተወሰነ ውጤት ቢኖር ኖሮ፤ ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ገለልተኛ ታዛቢዎችን፣ 65,299 የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ታዛቢዎችን ወይም 1,100 ዕውቅና የተሰጣቸውን ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች መጋበዝ ባላስፈለገ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ሀገራዊ ምርጫ ለተሳተፉ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ላሠማራቸው ከ350,000 በላይ ኃላፊዎች፣ ሂደቱን ለጠበቁት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ግንባታ መጎልበት እና ለሂደቱ መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት ላረጋገጡት የአፍሪካ እና ቀጣናዊ የታዛቢ ቡድኖች ምስጋናቸውን ያቀርባሉ!
ስለ ኢትዮጵያ ልማት
ኢትዮጵያውያን ግንቦት 24 2018 ዓ.ም ውሳኔያቸውን ሲያስቀምጡ፣ ሀገራቸውን በፍጹም የዴሞክራሲ ባህል ውስጥ ለማንበር ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ባላት ጸጋ ልክ የሚያስፈልጋትን ሁለንተናዊ ልማት በፍጥነት እውን የማድረግ ባህል እንዲቀጥል ሕዝባችን ተናግሯል።
ባለፉት ዓመታት የታየው እውነት እንደሚያሳየን የኢፌዴሪ መንግሥት የተስፋ ቃል መንግሥት አልነበረም። ይልቁንም በተጨባጭ የሚታዩ ውጤቶች የተመዘገቡበት ውጤት ተኮር መንግሥት ሲሆን፤ እነዚህም ውጤቶች በግልጽ የሚታዩ ናቸው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት የ9.2 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፥ ይሄም በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ኢኮኖሚዎች አንዱ ያደርገዋል። ይሄንን መነቃቃት መሠረት በማድረግ በ2018 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገቱ 10.2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ዕድገቱ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪንና የአገልግሎት ዘርፎችን በከፍተኛ ደረጃ ያካተተ ሰፊ መሠረት ያለው ቢሆንም፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ኢንዱስትሪው ለዕድገቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ እየመጣ ይገኛል። ይሄም መንግሥት ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለዕሴት ጭማሪና ለውጭ ገበያ ተኮር ምርቶች የሰጠውን ቀጣይነት ያለው ትኩረት ያሳያል።
እነዚህ ውጤቶች እንዲሁ ግምቶች ብቻ ሳይሆኑ፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሥርዓት አማካኝነት ክትትል የሚደረግባቸው የተጠያቂነትና የታቀደ አመራር ፍሬዎች ናቸው። አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 20 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ይህም ከ2016 ዓ.ም. ወዲህ የ100 በመቶ ገደማ ጭማሪ አሳይቷል። የዋጋ ግሽበትም ወደ ታች ማሽቆልቆሉን በመቀጠል አሁን ላይ ወደ አንድ አሐዝ ደረጃ እየተቃረበ ይገኛል፤ ይሄም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በቤተሰቦችና በንግዶች ላይ ከባድ ጫና ፈጥሮ ከነበረው ባለ ሁለት አሐዝ የዋጋ ግሽበት አንጻር ትልቅ መሻሻል ነው። ይህ ስኬት የተመዘገበው ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ቁሳቁሶችን ገበያ ያናጋው የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ጨምሮ፣ ውጫዊ ጫናዎች በነበሩበት ወቅት ነው።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ከተጀመረ ወዲህ መንግሥት ከውጭ ምንጮች ምንም ዓይነት አዲስ የንግድ ብድር ስምምነት ያላደረገ ሲሆን፥ ይሄም የሀገሪቱን የብድር ዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ አቅልሎታል። ከእነዚህ ቁጥሮች በስተጀርባ ኢትዮጵያውያን በዓይናቸው የሚያዩትና በእጃቸው የሚዳስሱት ተጨባጭ ለውጥ አለ። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለንግድ ተቋማትና ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ ይገኛል። ይህ ግድብ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን የተደገፈ፣ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች የተገነባና ቀጣይነት የነበረውን ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ የተጠናቀቀ ነው። ከሃይድሮ ፓወር ጎን ለጎን፥ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚገኘውን የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ እና በአርሲ ዞን የሚገኘውን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፤ በመሳሰሉ ሥራዎች የታዳሽ ኃይል አቅርቦቷን እያሰፋች ሲሆን፥ ይህም የቀጣናዊ ኢነርጂ ትብብርን እያሳደገ የብሔራዊ ኃይል አቅርቦት መረቡን የመቋቋም ዐቅም ያጠናክራል። በአፍሪካ አህጉር ታሪክ ውስጥ ትልቁ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት አንዱ የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ተጀምሯል። እነዚህ ምኞቶች አይደሉም፤ ተጨባጭ ሐቆች ናቸው።
ግብርና፣ አምራች ኢንደስትሪና ቴክኖሎጂ
በግብርናው ዘርፍ፣ የመንግሥት የምግብ ሉዓላዊነት አጀንዳ ወቅታዊ ለውጦችን ሳይሆን መዋቅራዊ ውጤቶችን እያስገኘ ቀጥሏል። በሶማሌ ክልል የጎዴ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካን ለመገንባት ከአሊኮ ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር የተፈረመው አጋርነት የዘመኑ ጉልህ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ማረጋገጫ ነው። ፋብሪካው በዓመት 3 ሚልዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የማምረት አቅም እንዲኖረው ታቅዶ እየተገነባ ሲሆን፥ ይሄም ኢትዮጵያን በዓለም ትላልቅ ማዳበሪያ አምራች ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. የፕሮጀክቱን የግንባታ ሂደት በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ “ይህ ፕሮጀክት በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በምግብ ዋስትና፣ በኢንዱስትሪ ዕድገትና በኢኮኖሚ ራስን መቻል ላይ የተደረገ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው” ብለዋል። አስተማማኝ ባልሆነና ውድ በሆነ የማዳበሪያ አቅርቦት ለረጅም ጊዜ ለተገደቡት ኢትዮጵያውያን አምራቾች የዚህ ፕሮጀክት ፋይዳ ፈጣንና ተጨባጭ ነው።
ከዚህ ምርጫ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ ምርቃት ላይ ሲገኙ የታየው ተምሳሌትነት ለቦረና ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ይህ ዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅበት ስም የሀገርን አንገት ያስደፋ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሲሆን፤ እርሱም ድርቅ ነው። ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የዝናብ መጥፋት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶችን የገደለ፣ ቤተሰቦች ለውኃ ፍለጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዙ ያስገደደ፣ እንዲሁም በእነዚህ የግጦሽ መሬቶች ላይ ለዘመናት ራሳቸውን ችለው የኖሩ ማኅበረሰቦችን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እጅ እንዲዘረጉ አድርጎ ነበር። ዓለም የሚያውቃት ቦረና እርሷ ነበረች። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንቦት ወር ጉብኝት ግን የተለየ ታሪክ አሳይቷል። አሁን ላይ ለአርብቶ አደር ማኅበረሰቦችና ለከብቶቻቸው ንጹሕ ውኃ እያቀረቡ ያሉትን የውኃና የመስኖ መሠረተ ልማቶችን የገመገሙ ሲሆን፥ ከጥቂት ዓመታት በፊት አቧራ ብቻ በነበረው መሬት ላይ የክላስተር እርሻዎችን ጎብኝተዋል፤ በያቤሎ የባህል ማዕከል መርቀዋል፤ እንዲሁም በአየር ንብረት ሁኔታዎች ምክንያት ቀድሞ ተገልሎ ለነበረው ቀጣና ዓመቱን ሙሉ ትስስር የሚፈጥር አውሮፕላን ማረፊያ መርቀው ከፍተዋል።
የአምራች ዘርፉም ተመሳሳይ የለውጥ ታሪክ አለው። በግንቦት 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 4ኛው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ፤ መንግሥት ለአራት ዓመታት የተመዘገበውን ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ መስፋፋት ውጤቶች አቅርቧል። የአምራች ዘርፉ የግብአት አቅርቦት በዓመት 9 ሚልዮን ቶን ወደ 15 ሚልዮን ቶን አድጓል። የምርት አቅም አጠቃቀም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ የማኑፋክቸሪንግ ዕድገት ከ4.8 በመቶ ወደ 10.7 በመቶ ማደጉን፣ እንዲሁም ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበው ፋይናንስ ከ8.1 ቢልዮን ብር ወደ 50 ቢሊዮን ብር ማደጉን ያሳያል። እነዚህ ስኬቶች በሀገር ውስጥ ምርት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንጸባረቁ ይገኛሉ። ኤክስፖው በተጠናቀቀ በሃያ ቀናት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ተጠናቆ ከ80 በመቶ በላይ ጥሬ ዕቃውን ከሀገር ውስጥ የሚያገኘውን ግዙፍ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት «ግራንዲዩር የሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ» ፋብሪካን በሞጆ ከተማ መርቀዋል። ቀደም ሲል በገቢ የሴራሚክ ምርቶች ላይ ጥገኛ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሴራሚክ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ ለማቆምና ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት ለማስፋፋት እየተዘጋጀች ትገኛለች።
በቴክኖሎጂው ዘርፍም፥ ዘመናዊ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዳታ፣ በፈጠራና በዲጂታል ሥርዓቶች የሚወሰን መሆኑን በመገንዘብ፥ መንግሥት ኢትዮጵያን ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የኢንዱስትሪ 5.0 ማሕቀፎችን ቀድመው ከተገበሩ ሀገራት ተርታ እያሰለፋት ይገኛል።
የጽንፈኝነትን ፖለቲካ ውድቅ ማድረግ
በኦነግ ሸኔ ዐማጽያን በንጹሐን ዜጎች ላይ በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ዒላማ ተደርገው የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ፤ የቤተሰብ እና የወዳጆቻቸውን ሕይወት ላጡ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና የቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው በአርሲ ዞን ለሚገኙ ወገኖቻችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻሉ።
እነዚህ ጥቃቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ዕድገት ለማደናቀፍ ከሚሹ አካላት፣ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ አማፂ ቡድኖች እና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ጥላቻ ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በጥምረት የተከናወኑ ሲሆኑ፤ ዓላማቸውም በኢትዮጵያ አለመረጋጋትንና የምርጫ መስተጓጎልን ለመፍጠር ሲደረግ የነበረ የጥፋት ውጥን ተከታይ ነው። መንግሥት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር ፍትሐዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ልዩ ትኩረትና ዝግጅት በማድረግ በቁርጠኝነት ሲሠራ ቆይቷል። በሌላ በኩል የጥፋት ኃይሎች ከባዕዳን ጋር 'ፅምዶ' የሚል ቁርኝት በመፍጠር ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ሰፊ የጥፋት ዝግጅት ሲያድርጉ ቆይተዋል፣ ሀገራዊ ምርጫው እንዳይከናወን ሰፊ ርብርብ አድርገዋል። በተጨባጭም በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የዜጎችን የመምረጥ መብትና ነጻነት ለመጋፋትና ለማደናቀፍ አለን የሚሉትን የጥፋት እጅ ዘርግተዋል።
እነዚህ የጠላት ኃይሎች በመደጋገፍና በመናበብ ዐመፅና ሁከት ለማነሳሳት፣ ከተሞችን በሽብር ጥቃት ለማወክ፣ በመንገዶች የደፈጣ ጥቃት በመፈጸም እንቅስቃሴ ለመገደብ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ዒላማ አድርገው ነጥሎ ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል። እንደ ማሳያ የጦር መሣሪያ፣ ተተኳሾችንና ሌሎች ሎጀስቲክሶችን በድጋፍ በማቅረብ በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አዋሳኝ የአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትንኮሳ ፈጽመዋል፣ በአማራ ክልል ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና ወልድያ ከተሞችን ጨምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እና ሲቪሎች ላይ ዒላማ በማድረግ ያካሄደው የሽብር እንቅስቃሴና ዝግጅት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባደራጃቸው የኅቡዕ ሴሎች አማካኝነት በተመረጡ አከባቢዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ተንቀሳቅሰው የነበረ ቢሆንም ይሄን የጥፋት ሴራ እና ድርጊት እንዲከሽፍ ማድረግ ተችሏል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሸኔ ሽብር ቡድን ከጽንፈኛው ፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር በመናበብ በአንዳንድ አካባቢዎች መንገዶችን በመዝጋት እንቅስቃሴ ለማስቆምና ለማስተጓጎል ፍላጎት የተንቀሳቀሰ ቢሆንም በጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት የተጠናከረ እርምጃ ፍላጎቱን ማሳካት አልቻለም። ቡድኑ በፀጥታ ኃይሉ የተወሰደበትን ርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ እና ፍላጎቱን ማሳካት ባለመቻሉ ስስ ዒላማዎች ላይ ያተኮረ ርምጃ በመውሰድ የሃይማኖት እና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ በማለም በአርሲ ዞን አሰኮ እና አካባቢው ጥቃት በመፈጸም ሁሉን አይነት የጥፋት ርብርብ ያደረገ ቢሆንም ሁኔታውን በመቆጣጠር ፀጥታ ኃይላችን በእነዚህ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ ርምጃ እየወሰደ ይገኛል።
መንግሥት መሰል ሥጋቶችን በንቃት በመከታተል ላይ ሲሆን፣ በምርጫው ወቅትም በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀነባበሩ ተመሳሳይ ዕቅዶችን በስኬት ማክሸፍ ችሏል። በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን፤ ፍርሃትና ክፍፍልን ከሚያጎሉ የሚዲያ ዘመቻዎች ጋር በማስተሣሠር የተቀነባበረው ይህ እኩይ ተግባር፤ በመንግሥት የደኅንነት መዋቅርና ኦፕሬሽኖች አማካኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስተጓጎል ተደርጓል። ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ ክፍፍልን ለመዝራት የኃይል ጥቃትን እና ውድመትን እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙ አካላት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በግልጽ ሊወገዙ ይገባል። መሰል ተግባሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የወደፊት ዕድል እንደሌላቸው ለማሳየት የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ በመስጠት ወሳኝ ርምጃዎችን ይቀጥላል።
በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት፣ ድርጊታቸውን ምክንያታዊ ለማስመሰል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ንግግር ቢጠቀሙ፤ ወሳኝ ዓላማን እያሳኩ ሳይሆን ወንጀል እየፈጸሙ ነው። የፖለቲካ ቅሬታዎች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ በብሔራዊ ምክክር ሂደት እና በዴሞክራሲያዊ ተቋማት አማካኝነት መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ እና ሊያገኙ የሚገባቸው ናቸው።
Click here to claim your Sponsored Listing.
Category
Contact the business
Telephone
Address
Addis Ababa