AWRA AMBA
The Awra Amba community thought a lot and changed harmful traditional practices exercised in Ethiopia and other countries in different parts of the world.
18/05/2026
ልጄ ይሄንን ነካ፣ ይሄን አደረገ፣ እንዲህ ይሆናል ብየ አልጨነቅም!
የልጆች አስተዳደግ እና የነገ ማንነታቸው የሚወሰነው ዛሬ በምናስቀምጥላቸው መሰረት ላይ ነው። በአውራ አምባ ማህበረሰብ ህጻናት ገና በለጋ እድሜያቸው ወደ የህጻናት መዋያ (መዋዕለ-ህጻናት) ሲገቡ፣ ከቀለም ትምህርቱ በተጨማሪ ማህበራዊ እሴቶችን ቀስመው እንዲያድጉ ትልቅ በር ይከፈትላቸዋል።
በዚህ የህጻናት መዋያ ውስጥ ትልቁ እና ዋነኛው ትኩረት ስነ-ምግባር ላይ ነው። ህጻናት እርስ በርስ እየተጫወቱ ስለ ማህበረሰቡ ህይወት፣ ስለ እኩልነት እና ስለ ሰው ምንነት ጥልቅ እውቀት እያገኙ ያድጋሉ።
ይህ የህጻናት ት/ቤት ለልጆች ብቻ ሳይሆን ለወላጆችም ትልቅ እፎይታ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን በታመነ፣ አስተማማኝ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ላይ ማድረጋቸውን ሲያውቁ፣ ስራቸውን በሙሉ ትኩረት፣ በሰላምና በስርዓት ለማከናወን ሙሉ እድል ያገኛሉ። ልጄ የት ሄደች? ምን አጋጠማት? አደጋ እንዳይደርስባት የሚል ስጋት ሳይኖር፣ በዕረፍት ሰዓት ሄዶ በማየትና በመንከባከብ፣ የዕለት ተዕለት ስራን በስኬት መወጣት ያስችላል።
ህጻናት ማህበረሰቡ የሚናገረውንና የሚያደርገውን እያዩ፣ ድርጊቶችን እየቀዱ ነው የሚያድጉት። ስለዚህ ወላጆችና ማህበረሰቡ በተግባር የሚያሳያቸው መልካም ምግባር እና በትምህርት ቤት የሚያገኙት ስነ-ምግባር ተዳምረው ሁለንተናዊ ስብዕናቸው የተገነባ ህጻናትን ማፍራት ተችሏል።
ሙሉ ቪዲዮውን ለመመልከት https://youtu.be/0DLF41tBwxY
04/05/2026
እኛ የመጨረሻዎቹ ነዋሪዎች አይደለንም!
የቀደሙት አባቶቻችን ስለ ሀገራችን ተፈጥሮ ሲተርኩ፣ ምድሪቱ በትልልቅ ዛፎች የተሸፈነች፣ በዱር አራዊትና በአዕዋፍ ዝማሬ የተዋበች፣ እንዲሁም በፈሳሽ ወንዞችና በለመለሙ መስኮች የታጀበች እንደነበረች ይነግሩናል። ዛሬ ላይ በፊልሞችና በዶኩሜንታሪዎች እንደምናየው ድንቅ ስዕል፣ ያኔ የነበረው እውነታ ለሰሚው በምናብ የተፈጠረ ተረት ይመስላል። ነገር ግን ያ ተረት ሳይሆን የነበረና የጠፋ ሀብታችን ነው።
ዛሬ ላይ ክረምቱን በሃይል ሲፈስ የነበረ ወንዝ ገና በህዳርና በታህሳስ ሲደርቅ እናያለን። የደን ሽፋናችን ተመናምኖ ወደ በረሃማነት ሲቀየር፣ የአራዊቱና የአዕዋፋቱ ድምፅ እየራቀን ሲሄድ ይታወቃል። ይህ በንፅፅር ሲታይ እጅግ የሚያስደነግጥ የተፈጥሮ ሀብት ውድመት ውስጥ መሆናችንን ያሳያል።
ዛሬ ላይ ያጣነው ሀብት እንዲህ ከሆነ፣ የነገው ትውልድ እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል?
እኛ የዚህች ምድር የመጨረሻ ነዋሪዎች አይደለንም። ተፈጥሮን እንደማያልቅ የሀብት ምንጭ ቆጥረን በግዴለሽነት ያለአግባብ መጠቀም፣ የወደፊቱን ትውልድ ህይወት ማቀጨጭና ተስፋውን መቅበር ነው።
ዛሬ ላይ ዛፎችን በመትከልና በመንከባከብ፣ የውሃ ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም፣ የተፈጥሮ ማዕድናትንና ሌሎች ፀጋዎችን ለነገው ትውልድ በሚተርፍ መልኩ በቁጠባ መጠቀም ብቸኛው መፍትሄ ነው።
ተፈጥሮን ለትውልዱ እናቆይ!
ሙሉ ቪዲዮውን ለመከታተል https://youtu.be/4zKwVpN0Ixg
06/04/2026
እኛ ታዳጊ ህጻናቶች የሰውን ገንዘብ አንነካም!
የአንዲት አገር የወደፊት ብሩህነት የሚወሰነው ዛሬ በምናፈራው ትውልድ ስብዕና ላይ በመሆኑ፣ አገር በቀል እውቀትንና መልካም ስነ-ምግባርን በህጻናት ልቦና ውስጥ መዝራት የነገ አቅኝዎችንና ባለውለታዎችን የማፍሪያ ዋነኛ መንገድ ነው። ዛሬ የምንዘራው በጎነት የማህበረሰቡን ኑሮ የሚቀይሩ ዜጎችን የሚገነባ ቢሆንም፤ በተቃራኒው ህጻናት ክፋትን፣ መጥፎ ተግባራትንና አጸያፊ ንግግሮችን እየተማሩ ካደጉ ግን የአገር ተስፋን ከማጨለሙም በላይ ወላጆችንና ማህበረሰቡን ለማይወጣው ቀውስ ይዳርጋሉ።
ይህንን እውነታ በጥልቀት የተረዳው የአውራ አምባ ማህበረሰብ፣ ህጻናትን ከመጥፎ አሰራርና አነጋገር በማራቅ በበጎ እሴቶችና በታላቅ የሃላፊነት ስሜት እንዲያድጉ የሚያደርገው ጥረት፣ ለነገዋ አገር ተስፋ የሚሆን ጠንካራ ትውልድ ለመገንባት የሚደረግ የላቀ ተግባር ነው። በአውራ አምባ ህጻናት እግረ-ተከል ከሆኑ ጀምሮ ማህበረሰቡ ባዘጋጀው የመዋለ-ህጻናት ት/ቤት በማህበረሰቡ አባላት በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ፣ ፊደሎችን እንዲለዩና ወደ መደበኛ ት/ቤት ከመግባታቸው በፊት ማዎቅ የሚገባቸውን ሁሉ እንዲያውቁ ይደረጋል።
ህጻናቱም ተምረው ከት/ቤት ሲወጡ በየቀኑ የሚያሰሟት መፈክር አለቻቸው።
"እኛ ታዳጊ ህጻናቶች የሰውን ገንዘብ አንነካም፣
ወድቆ ብናገኝ ለባለቤቱ እንመልሳለን፣
በመተባበር በመተዛዘን እየሰራን እናመርታለን፣
የሰላም ኑሯችን ይለመልማል።"
ይህቺ መፈክር በህጻናቱ ልቦና ውስጥ በጉልህ ታትማለች። የአውራ አምባ ማህበረሰብ የሰው ገንዘብ መብላት ወንጀል ነው ፤ ከወንጀልም አልፎ እርም ነው ብሎም ያምናል። ስለሆነም ህጻናቱ በዚህ እሴት ታንጸው እንዲያድጉ ከልጅነታቸው ጀምሮ ት/ት ይሰጣቸዋል ማንኛውንም ወድቆ ያገኙትን ንብረት ለባለቤቱ አፈላልጎ መስጠት እንዳለባቸውም ጠንቅቀው ያውቃሉ።
እስኪ ምንያክሎቻችን ልጆቻችንን በመልካም እሴት ታንጸው እንዲያድጉ ክትትል እናደርጋለን? ከሌብነት፣ ከስድብና መሰል መጥፎ ስራዎች ንጹህ ሆነው እንዲያድጉ ምክርና ትምህርትስ እንሰጣቸዋለን?
እኚህ ህጻናት በስነ-ምግባር ተኮትኩተው የነገ ሃገር ተረካቦዎች እንዲሆኑ በዋናነት "ስነ-ምግባር" የተሰኘ ት/ት ይሰጣቸዋል። ከዚህም ባለፈ በቀለም እውቀታቸው የተሻሉ ይሆኑ ዘንድ የአማርኛ፣ የእንግሊዝኛ እና የሂሳብ ት/ትንም ይወስዳሉ።
የመዋለ ህጻናቱን ሙሉ የውሎ እንቅስቃሴ ለመመልከት https://youtu.be/2BkqYZzzhTc
Click here to claim your Sponsored Listing.