Yonas Tade
ይህ ቻናል መንፈሳዊ መልእክቶች እና ዝማሬዎች ይተላለፉበታል:
07/12/2026
ሁለቱ ደማቆች (ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ)
ቤተ ክርስቲያን የእነዚህን ሁለት ቅዱሳን የሰማእትነት እለት ሰማእትነትን በተቀበሉበት በተመሳሳይ እለትና በተለያዩ ዓመታት በሐምሌ 5 ቀን ትዘክራቸዋለች፡፡ ታስባቸዋለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየ ዓመቱ ሐምሌ 5 ቀን “በዓለ ሐዋርያት” በማለት ታከብራለች፡፡
ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሁለት ሐዋርያት በኩራት ታከብራቸዋለች፡፡ በሚገባም ታመሰግናቸዋለች፡፡ በተለይ በጾመ ሐዋርያት ወቅት ልዩ ክብር ከመስጠትዋ በላይ በፍጹም ትህትና የጾመ ሐዋርያትን ፍቺ ሰማእትነት በተቀበሉበት እለት በሐምሌ 5 ቀን አድርጋዋለች፡፡
እነዚህ ሁለት ቅዱሳን በስብእናቸው፣ በአገልግሎታቸው እና ባላቸው ጠባያት ሁለት የተለያዩ ባሕርያትን የያዙ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆኑ የተለያዩ መለያዎች አሏቸው፡፡
ከአጠራራቸው እስከ ትምህርታቸው
ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ከእርሱ ጋር እንዲያገለግሉ ከጠራቸው ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱና የመጀመሪያው ነው፡፡ (ማቴ 10)
ቅዱስ ጳውሎስ ግን ከአስራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ሆነ ከሰባ ሁለቱ አርድእት (የወንድ አገልጋዮች) መካከል አልነበረም፡፡ ከትንሳኤው፣ ከእርገቱ እና ከማትያስ መመረጥ በኋላ በመጨረሻው የምርጫ ወቅት ጌታ ለአገልግሎት ጠራው፡፡ ጌታ በምድር በስጋው ወራት ሳለ የክርስቶስ ተከታይ አልነበረም፡፡ ስለዚህም መጠራቱ ሲናገር እንዲህ አለ “ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ፡፡ እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፡፡ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድኩ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም” (1ኛ ቆሮ 15÷8-9)
ቅዱስ ጳውሎስ ምንም እንኳን ለአገልግሎት ከተጠሩት ሐዋርያት መካከል የመጨረሻው ቢሆንም ከሁሉ ይልቅ በብዙ የደከመ እርሱ ነው፡፡ “ከሁላቸው ይልቅ እኔ ደከምሁ” (ቁ. 10) ይህም የሚያሳየው በክርስትናና በክርስቶስ ቤት ውስጥ ትልቁ ነገር ፊት የመምጣትና ኋላ የመቅረት ወይንም የመከተል ጉዳይ ሳይሆን ለተጠሩበት የወንጌል ሕይወት ብቁ ሆኖ መገኘቱ ላይ ነው፡፡ ምዘናው እሽቅድምም ሳይሆን በእርጋታ ሮጦ በማስተዋል በእምነት መጨረሱ ላይ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በቤተ ሳይዳ ሲሆን ወላጆቹ ደግሞ የኖሩት በቅፍርናሆም ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የተወለደው በኪልቂያ አውራጃ በጠርሴስ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ የልጅነት እድሜው የጀመረውን የሐይማኖት እና የህግ ትምህርት ከታወቀው ሊቅ ለማጠናቀቅ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ (የሐዋ. ስ. 22÷3)
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በህግ (በጋብቻ) ተወስኖ ኖረ ነው፡፡ በጋብቻ ተወስኖ ስለመኖሩም ቅዱስ ወንጌል ጌታ የቅዱስ ጴጥሮስን አማት ከንዳዷ እንደፈወሳት ይናገራል፡፡ አማት ሲል የሚስት እናት ለማለት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ (ማቴ 8÷14-15) ቅዱስ ጳውሎስ በወንጌል አገልግሎት ጉዞው “እንደ ኬፋ (ጴጥሮስ) እህታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን” በማለት አብርሃም ሳራን እህቴ ብሎ በጠራው አጠራር አንጻር ጴጥሮስ ሚስት እንዳለው ጠቁሟል፡፡ (1ኛ ቆሮ 9÷5)
ሁለቱም አይሁዳውያን ነበሩ
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለራሱ ሲናገር ከቢንያም ነገድ የወጣ አይሁዳዊ እንደሆነ ጸፏል፡፡ (ፊል 3÷5)
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሐዋርያው ጴጥሮስ ከየትኛው ነገድ እንደሆነ አልተናገረም፡፡
ሁለቱም በጌታ የተጠሩ ናቸው
ጴጥሮስ በጌታ የተጠራው (ማቴ 4÷ 18-20)
ጳውሎስ በጌታ የተጠራው (የሐዋ. ስ 9÷ 1- 4)
ምንም እንኳን ሁለቱም ሐዋርያት በእግዚአብሔር የተጠሩ ቢሆንም አጠራራቸው ግን ለየቅል ነበር፡፡ ጴጥሮስ በክብር ጳውሎስ በግዴታ፡፡
ጌታ ይጠሩበት የነበረውን የሁለቱንም ስም ቀይሮታል፡፡
ጴጥሮስ የዮና ልጅ ስምዖን እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ (ዮሐ 21÷15) ጌታም ጴጥሮስ ተብሎ እንዲጠራ ሕይወቱን እንደለወጠው መጠሪያውንም ለወጠው፡፡ (ማቴ 16÷17-18)
የሳውልም ስም ተለውጦ ጳውሎስ ተባለ፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ በደማስቆ ጎዳናው ሲጓዝ ሳለ ሲጠራው ሳውል እያለ ጠርቶታል፡፡ (የሐዋ. ስ 9÷4) ከተመረጠና ከተጠራ በኋላ ደግሞ ጳውሎስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ (የሐዋ. ስ 23÷11)
መንፈስ ቅዱስ በሁለቱም ላይ አደረባቸው፡፡ ሁለቱም በልሳናት ተናገሩ፡፡
መንፈስ ቅዱስ በበአለ ሃምሳ እለት በሐዋርያቱ ላይ በወረደ ጊዜ እርግጥ ነው ቅዱስ ጴጥሮስ ከ 70 የሚበልጡ ቋንቋዎችን ተናግሯል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ የሚከተለውን ከትቧል “ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” (1ኛ ቆሮ 14÷18)
ሁለቱም ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን የማሳደር (ጸጋ) ነበራቸው
የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ስላወቁ ጴጥሮስና ዮሐንስ “እጃቸውን ጫኑባቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ” (የሐ 8÷17)
ቅዱስ ጳውሎስም የኤፌሶን ሰዎች ከተጠመቁ በኋላ “እጁን ጫነባቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ወረደባቸው፡፡ በልሳኖችም ተናገሩ” (የሐዋ. ስ 19÷5-7)
ሁለቱም ታላላቅ ተአምራቶችንና ድንቆችን አደረጉ
“እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፡፡ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር፡፡ ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር” (የሐዋ. ስ 19÷11)
ሁለቱም የሞተ አስነስተዋል
ሐዋርያው ጴጥሮስ የሞተችዋን ነፍስ ዘራባት፡፡. ጴጥሮስም ተንበርክኮ ጸለየ፡፡ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ ፡- ጣቢታ ሆይ ተነሺ አላት፡፡ እርስዋም አይኖችዋን ከፈተች፡፡ . . . እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሳት፡፡” (የሐዋ. ስ 9÷36-41)
ሐዋርያው ጳውሎስም ከሞት አስነሳ፡፡ “. . . . አውጤክስ የሚሉት አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፡፡ . . . . እንቅልፍም ከብዶት ከሶስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፡፡ ሞቶም አነሱት፡፡ ጳውሎስም በላዩ ላይ ወደቀ፡፡ አቅፎም አትንጫጩ አላቸው፡፡ . . . ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት፡፡ እጅግም ተጽናኑ” (የሐዋ. ስ 20÷7-12)
ሁለቱም የጋለ ፍላጎት፣ ብርቱ ኃይል እና የማሻገር ጸጋ ነበራቸው፡፡
ሁለቱም ሙሉ ጉልበታቸውን ለአገልግሎት የሰጡ፣ ብርቱ ተናጋሪዎችና ሰባኪዎች ነበሩ፡፡ (የሐዋ. ስ 9÷22፣31) (የሐዋ 10) ለተሰደዱትና መጻተኞች ለነበሩት አይሁድም ሰበከላቸው፣ ደብዳቤም ላከላቸው “በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ መጻተኞች. . . ” (1ኛ ጴጥ 1÷1)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ከሁላቸው (ከሐዋርያቱ) ሁሉ ይልቅ ደከመ” (1ኛ ቆሮ 15÷10)
ሁለቱም በአገልግሎታቸው ደፋሮችና ጸኑዎቸ ነበሩ
ቅዱስ ጴጥሮስ “የአብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ የአባቶቻችን አምላክ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቆርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው፡፡ እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፣ የህይወትንም ረስ ገደላችሁት፡፡” (የሐዋ. ስ 3÷13-15)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ክርስቶስን በሚቃወሙት በገዢዎች ፊት ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ደፋር ነበር፡፡
ጳውሎስም “ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኩነኔ ሲነጋገር ሳለ ፊልክስ ፈርቶ. . . ” (የሐዋ. ስ 24÷25) በንጉሱ ግሪጳም ፊት ተከሶ በቀረበ ጊዜ እንዲህ አለው “ንጉስ አግሪጳ ሆይ ነቢያት ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ፡፡ አግሪጳም ጳውሎስን በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ አለው፡፡ ጳውሎስም በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ገድሞ ከዚህ እስራት በቀር እንደኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ አለው” (የሐዋ. ስ 26÷27-29) (የሐዋ. ስ 22÷25-29) (የሐዋ. ስ 25÷10-12)
ሁለቱም ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ እግዚአብሔርን የሚበድሉትን ኃጢአተኞች በመቅጣት የማያወላውል ጠንካራ አቋም ነበራቸው
ቅዱስ ጴጥሮስ (የሐዋ. ስ 5÷1-11) (የሐዋ. ስ 8÷18-22)
ቅዱስ ጳውሎስም በቆሮንቶስ ኃጢአተኞ ላይ ጠንካራ አቋም ነበረው፡፡ ባደረው ነገር ሲገስጸውም አንዳች ነገር አልፈራም ነበር፡፡ (1ኛ ቆ 5÷3-5፣13) (የሐዋ. ስ 13÷6-11)
ሁለቱም ሐዋርያት ትሁታን ነበሩ
ቅዱስ ጴጥሮስ አሳ ከሚያጠምድበት ስራው በተአምር ካላሰበው የመንፈስ ስራ ላይ እንዲውል በጌታ ጥሪ ከተጠራ በኋላ በፍጹም ትህትና ሆኖ የተመረጠበት ስራ ከእርሱ ለተሻሉ እንዲሰጥ እርሱ ግን ይህን ሰማያዊ ጥሪ እንደማይመጥን ኃጢአቱን እያሰበ በኢየሱስ እግር ስር ወድቆ እንዲህ አለ “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከእኔ ተለይ” አለው፡፡ (ሉቃ 5÷8)
ስለ ቅዱስ ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን አዋልድ መጻህፍት እንደሚሉት ሰማእትነትን ለመቀበል ወደ ንጉስ ኔሮን አደባባይ በወጣና ሊሰቅሉት ንጉሱ በፈረደበት ጊዜ ምናልባት እንደ ጌታዬ ይሰቅሉኝ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ ክብር እና እንደ እርሱ ልሆን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ከእርሱ የማንስና ክብርም የማይገባኝ ነኝ፡፡ ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ እንጂ እንደ ጌታዬ ክብር ያለውን ስቅላት አልሰቀልም በማለት ራሱን ዝቅ ያደረገና እንደለመነው ተዘቅዝቆ የተሰቀለ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም የቀደመ ክፉ ማንነቱን እያነሳ እንዲህ አለ “አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን ይህን (ክርስቶስ) አደረገልኝ፡፡ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ” (1ጢሞ 1÷13) ጌታ እንዴት እንደተገለጠለት ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈላቸው ደብዳቤው ራሱን ባዋረደ ትህትና ደግሞ እንዲህ አለ “ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ፡፡ እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ (ሰው) የሆንሁ እኔ ነኝ” (1ቆሮ 15÷8-10)
ሁለቱም ብዙ እንግልት፣ ፈተናና ስደት ደርሶባቸው ሰማእትነትን ተቀብለዋል
ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ተገረፈ፡፡ ወደ ወኅኒም ተጣለ፡፡
ሄሮድስ አይሁድን ለማስደሰት ሲል ቅዱሱን ያለ ምንም በደሉ በቁጥጥር ስር አዋለው፡፡ ወዲያውም “በያዘውም ጊዜ ወደ ወኅኒ አገባው፣ ከፋሲካም በኋላ ወደ ህዝብ ያወጣው ዘንድ አስቦ እያንዳንዱ አራት ወታደሮች ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍራ ክፍል አሳልፎ ሰጠው” (የሐዋ. ስ 12÷3-4) እንደ ሰው ክፋት ያልሆነውና ልጆቹ እንዲበደሉ የማይፈልገው አባት ግን በዚያን ሌሊት መልአኩን ልኮ ጴጥሮስን ከወኅኒ አስወጣው፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ላይ የደረሰው መከራ ግን እጅግ ብዙ ነው፡፡ በእርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን እርሱን አምነው አገልግሎቱን በተከተሉት ላይ ሁሉ ስደትና እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡
ስለዚህ ነገር ይህ ሐዋርያ እንዲህ አለ “ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፣ በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት በመጦም፣. . . . . ” (2ኛ ቆሮ 6÷4-6)
“በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፣ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፣ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፣ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፣ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በስጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በስጋችን ተሸክመን እንዞራለን፣ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ስጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሳ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና” በማለት አንዴ የሚደርስባቸውን ፈተናና እንግልት ሲጠቁም በሌላ መልኩ ደግሞ ከሞት በኋላ ስለሚገኘውም ዘላለማዊ የተስፋ ሕይወት ያስረዳል፡፡ (2ኛ ቆሮ 4÷8-11)
በመላው የአገልግሎት ዘመኑ የደረሰበትን በጥቅሉ በ 2ኛ ቆሮ 11 ላይ እንዲህ ሲል ማጠቃለያ ሰጥቷል ፡-
“በድካም አብዝቼ፣ በመገረፍ አብዝቼ፣ በመታሰር አትርፌ፣ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ፡፡ አይሁድ አን ሲጊድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ፡፡ ሶስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፣አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፣ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፣ ሌሊትና ቀን በባህር ውስጥ ኖርሁ፡፡ ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፣ በወንዝ ፍርሃት፣ በወንበዴዎች ፍርሃት፣ በወገኔ በኩል ፍርሃት፣ በአህዛብ በኩል ፍርሃት፣ በከተማ ፍርሃት፣ በምድረ በዳ ፍርሃት፣ በባህር ፍርሃት፣ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፣ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፣ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፣ በብርደና በራቁትነት ነበርሁ”
ሁለቱም ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ የሰማእትነትን አክሊል ተቀዳጅተዋል
ሁለቱም የምድራዊውን ህይወታቸውን ፍጻሜ ያገኙት የሮም ገዥ በነበረው ኔሮን ቄሳር እጅ በ 67 ዓ. ም አካባቢ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የቁልቁሊት ተሰቅሎ ሰማእትነትን ሲቀበል ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በሰይፍ አንገቱ ተቆርጦ አገልግሎቱን በክብር በሰማእትነት አጠናቋል፡፡
መምህር ፍጹም ታደሰ
በረከታቸው በእኛ ላይ ይሁን
“ክፉ እመልሳለሁ አትበል፤ እግዚአብሔርን ተማመን፥ እርሱም ያድንሃል።”
ምሳ 20፥22
07/05/2026
እግዚአብሔርን ማምለክ ከቅንነትና ከእምነት የሚወጣ አገልግሎት ነው። መገለጫውም ፍቅር ነው። ፍቅር ሲባል የራሱን የአምልኮ ክልል ሰዎች ብቻ መውድደና መንከባከብ ሌላውን መናቅና መርሳት እይደለም። አምነት እውነተኛ መሆኑ የሚረጋገጥበት አንዱና ትልቁ መስፈርት ፍቅር ነው። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም ተብሎ የተጻፈው ለዚህ ነው። ፍቅር ሰውን እንስሳትን ተፈጥሮን ሰማያውያንን እና እግዚአብሔርን መውደድ ነው። ፍቅር ሰፊ ክንፍ ነው። ስባራ ክንፍ አይደለም አንዱን አቅፎ አንዱን የተወ አይደለም። አያስመስልም። እውነተኛ ነው። እውነተኛ በመሆኑ ጥቃት ይደርስበታል። ግን ወርቅ መሬት ቢወድቅ ጸባዩ እንደማይለወጥ አይለወጥም።
እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት
ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም
Click here to claim your Sponsored Listing.