Christ Embassy Church - Summit 72

Christ Embassy Church - Summit 72

Share

ለህይወቶ ትርጉም ይሰጣል! giving your life a meaning

28/05/2026

RHAPSODY OF REALITIES
(Amharic) 🇪🇹🇪🇹🇪🇹

Thursday 28, May 2026
ሐሙስ፣ ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም.

📜 በመለኮታዊ ኃይሉ የተጠበቃችሁ
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

📖 “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና” (2 ጢሞቴዎስ 1:7)።

👤 ፓስተር ክሪስ
════════
የመክፈቻ ጥቅሳችን ፍርሃት የመንፈሳዊ ማንነታችሁ ወይም የተፈጥሯችሁ አካል እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል። ስለዚህ ፍርሃት ሊቆጣጠራችሁ ሲሞክር ከተሰማችሁ፣ እምቢ በሉት (አትቀበሉት)። መፅሐፍ ቅዱስን ስታጠኑ፣ በጥንት ዘመን ጌታ ለማንኛውም ሰው በተገለጠበት ጊዜ ሁሉ፣ ብዙ ጊዜ ፣ የመጀመሪያ ቃላቱ በኢሳይያስ 41:10፣ በኢያሱ 1:9 እና በራዕይ 1:17 ላይ እንደምታዩት “አትፍሩ” የሚል ነበር።

በዓለም ላይ ምንም ዓይነት ነገር ቢከሰት ፍርሃትን እንድንቃወም ያዘናል። እናንተ በሕይወታችሁ ላይ የእግዚአብሔር ማኅተም አለባችሁ፤ ይህም ከሚጎዳ ወይም ከሚያስር ከማንኛውም ነገር የሚለያችሁ መለኮታዊ አዋጅ ነው። እናንተ ለእግዚአብሔር የተለያችሁ ናችሁ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” (ዮሐንስ 3:16) የሚለውን የጌታን ቃል አስታውሱ።

ምክንያቱም የእርሱ የጥበቃ ማኅተም በእናንተ ላይ ስለሆነ ነው (ኤፌሶን 1:13)። ሁልጊዜም በድፍረት እንዲህ ብላችሁ አውጁ፦ “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?” (መዝሙር 27:1)።

እናንተ የደኅንነትን ክብር በውስጣችሁ ተሸከማችኋል። እናንተ ማምለጫ ፍለጋ፣ ወደ ችግር ውስጥ አትገቡም፤ ከማንኛውም ችግር ወይም አደጋ ጋር፣ ደኅንነት አብሮ አለ፤ መታደጋችሁ እርግጥ ነው። ተግዳሮቱ ከመገለጡ አስቀደሞ ፣ እናንተ ቀድማችሁ በድል ውስጥ ናችሁ። ስለዚህ በሕይወታችሁ፣ በአገልግሎታችሁና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችሁ ምንም ነገር እንዲያስፈራችሁ ወይም እንዲያስደነግጣችሁ አትፍቀዱ።

ሁኔታዎች አስጊ ቢመስሉም፣ ማንነታችሁን አስታውሱ፡- እናንተ ከአሸናፊዎች በላይ ናችሁ (ሮሜ 8:37)። ጌታ ራሱ ደኅንነታችሁ ነው። እናንተ በመለኮታዊ ኃይሉ የተጠበቃችሁ፣ በፊቱ የተከለላችሁ፣ እና ለዘለቄታው ድል የታጨችሁ ናችሁ። 2 ቆሮንቶስ 2:14 እንዲህ ይላል፡- “ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሳቱ ለሚያዞረን... ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።” ሃሌሉያ!

ስለዚህ፣ በድፍረትና በዓላማ ኑሩ፤ በሥልጣን ተናገሩ። ከዚህ ዓለም እንዳልሆናችሁ በመገንዘብ ተመላለሱ። በእናንተ ውስጥ ያለው ሕይወት ከማንኛውም ቀውስ የላቀ ነው፣ በእናንተ ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር መንፈስም ከጉዳት በላይ ይጠብቃችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በእናንተ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል” ይላል (1 ዮሐንስ 4:4)።

የእምነት አዋጅ
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ጌታ መጠጊያዬና ኃይሌ፣ መድኃኒቴም ነው፤ በእርሱም ከክፉ ነገር ሁሉ ተከልያለሁ እንዲሁም ተጠብቄአለሁ። በእኔ ውስጥ ያለው የእርሱ ሕይወት ከማንኛውም ቀውስ የላቀ ነው፤ ከሚጎዳ ወይም ከሚያስር ከማንኛውም ነገር በላይ ሁልጊዜም ከፍ አድርጎ ያኖረኛል። የኃይል፣ የፍቅር እና ራስን የመግዛት መንፈስ አለኝ። ሃሌሉያ!

ለተጨማሪ ጥናት
├─መዝሙር 27:1
├─ኢሳይያስ 41:10
├─1 ዮሐንስ 4:18


━━━━//━━━

27/05/2026

RHAPSODY OF REALITIES
(Amharic) 🇪🇹🇪🇹🇪🇹

Wednesday 27, May 2026
ረቡዕ፣ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም.

📜በሃገራት ላይ የእግዚአብሔርን ቃል አውጁ
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

📖 “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።” (1ኛ ዮሐንስ 5፡4)

👤 ፓስተር ክሪስ
════════
ዛሬ፣ በዓለም ውስጥ ለአገራት ምሪት ሰጪ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡ ስርዓቶችና ድምፆች አሉ፤ ነገር ግን ሐሳቦቻቸው ለብዙ አገሮች ውድቀት፣ መደናገር እና የኢኮኖሚ መመሰቃቀልን ነው ያመጡት። እነዚህ መፍትሄ እንሰጣለን ብለው የሚናገሩ ድርጅቶች ናቸው፤ ነገር ግን መሪዎችን አሳስተዋል፣ ኢኮኖሚዎችን ሽባ አድርገዋል፣ እና አገሮችን ወደ አላስፈላጊ ጥልቅ ዕዳ አስገብተዋል።

ብዙ መንግሥታት፣ በዓለም አቀፍ ችግር ጊዜ፣ ምንም ሳይለዩ እነዚህን ድምፆች ተከተሉ፤ ውጤቱም እጅግ የከፋ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እንደነዚህ ያሉ ተፅእኖዎች አስቀድሞ አስጠንቅቆናል፤ “እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል።” (1ኛ ዮሐንስ 4፡5)።

ነገር ግን ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን! በምድር ላይ ረዳት አልባ ሆነን የምንመለከት አይደለንም። እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ እኛ ሥልጣን አለን፤ እንገዛለን እናም ነገሮችን እንቀይራለን። በጸሎታችን እና በእምነታችን ሥራ የጨለማ ዕቅዶችን ማፍረስ እንችላለን። እኛ በቦታችን እስካለን እና በእምነት እነሱን ተቃውመን እስከቆምን ድረስ፣ ምንም አይነት ድርጅት፣ ሀሳብ ወይም መዋቅር አገራትን ሊቆጣጠር አይችልም።

ኃላፊነታችን በመንፈስ መቆም እና ቃሉን በአገሮችና በመሪዎቻቸው ላይ ማወጅ ነው። ሰላሙንና ብልጽግናውን በአገሮች ላይ አውጁ። እርሱም እንዲህ እንድናደርግ አዞናል፤ ሉቃስ 10፡5-6 “ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል።”

በስሙ ሃገሮችን ለመባረክ አስደናቂ ሥልጣን አለን፤ “በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤…” (ምሳሌ 11፡11)። በበረከት ቃላት፣ የዓለም ከተሞችና ሃገሮች ከፍ ከፍ ይላሉ። ካጭበርባሪዎች ባርነት፣ ከኢኮኖሚ ችግሮችና ከዕዳ ይነሳሉ፣ እና እግዚአብሔር ለእነርሱ ወዳቀደው ፍጻሜ ይገባሉ።

በእምነታችንና በምልጃችን፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ በምድር ላይ ያሸንፋል። ስለዚህ፣ ስለ ሃገራትና ስለ መሪዎቻቸው መጸለይ ቀጥሉ። እንደዚህ ስታደርጉ፣ የጨለማ ኃይሎችና ዕቅዶቻቸው ዝም ታሰኛላችሁ፣ ጽድቅም በሃገራት ውስጥ ይመሠረታል። መሪዎች እንዳይታለሉ፣ ሃገራቸውን ከሕገወጥና ከግፍ ዕዳ እንዲሁም ከክፉ ቁጥጥር ለማውጣት መለኮታዊ ጥበብ እንዲመራቸው አውጁ። ሃሌሉያ።

የእምነት አዋጅ
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ሃገራት ከማታለል ነጻ ወጥተዋል፣ መሪዎቻቸውም የእግዚአብሔርን ጽድቅ በምድራቸው ላይ ለማስፋፋትና ለመመስረት መለኮታዊ ጥበብን ይቀበላሉ። የዓለም ሃገራት ጠላቶች እቅዳቸው ፈርሷል፤ የኢየሱስ ስም ሥልጣን እና የክርስቶስ ድል በሁሉም ሃገራት ውስጥ ይፈጸማል። አሜን።

ለተጨማሪ ጥናት
├─1ኛ ዮሐንስ 5፡4
├─1ኛ ዮሐንስ 4፡4-5
├─ዳንኤል 4፡26

━━━━//━━━

21/05/2026

RHAPSODY OF REALITIES
(Amharic) 🇪🇹🇪🇹🇪🇹

Thursday 21, May 2026
ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም.

📜ትክክለኛውን ምክር ለማግኘት ቃሉን ተጠቀሙ
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

📖“ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር” (ማቴዎስ 16:21)

👤 ፓስተር ክሪስ
════════

ማቴዎስ 16 በጌታ በኢየሱስና በደቀ መዛሙርቱ መካከል ስለነበረ ወሳኝ ቅጽበት ይነግረናል። እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከሰበኩና ካወጁ
በኋላ፣ ጌታ ወደ ውስጥ በማተኮር፣ ሊመጣ ያለውን መግለጥ ጀመረ። ደቀ መዛሙርቱንም ማንነቱን ለጊዜው እንዳይገልጡ አዘዛቸው።

ከአፍታ በኋላ ወደ እየሩሳሌም እንደሚሄድ፣ ብዙ ስቃይ እንደሚያሳልፍ፣ እንደሚገደል እና በትንሳኤ እንደሚነሳ አብራራላቸው። ይህን ሁሉ ከሰሙ በኋላ፣ ጴጥሮስ የማይታመን ነገር አደረገ። መጽሐፍ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ገለል አድርጎ ወሰደና “….ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ። አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ።” ይላል (ማቴዎስ 16፡22)

እስኪ አስቡት፣ ጴጥሮስ ጌታን ሲገስጸው። በጴጥሮስ በኩል የሚናገረው ሰይጣን እንደሆነ ጌታ ያውቅ ስለነበር ለሰይጣን እንዲህ በማለት በቀጥታ ምላሽ ሰጥቷል፣ “….ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።” (ማቴዎስ 16፡23)

እነዚያን ቃላት በአንደበቱ ያስቀመጠው ሰይጣን እንደነበረ ስላላወቀ፣ ጴጥሮስ፣ በሁኔታው ሳይደናበር አልቀረም። ለማን እንደምትናገሩ ማወቅ ግድ ይላችኋል። የእግዚአብሔር የሆነን ነገር ብቻ ተወጡ። ሰይጣንን ለመደገፍ ድምፃችሁን አታውሱ።

ቃሉን ማወቅና አእምሯችሁን እንዲያድሰው ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው። ቃሉ በሙላት ይኑርባችሁ (ቆላስይስ 3፡16)። የእግዚአብሔር ቃል እውቀት መለየት እንድትችሉ ያደርጋችኋል፤ መልካሙን ከክፉ እንዲሁም በጎ፣ መልካምና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትናችሁ እንድታውቁ ያደርጋችኋል (ሮሜ 12፡2)። በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ከእናንተ፣ ከሰይጣን ወይም ከእግዚአብሔር የሚመጣውን መለየት ትችላላችሁ።

ጸሎት
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ውድ አባት ሆይ፣ መረዳት እና መለየትን ስለሚሰጠኝ ቃልህ አመሰግናለሁ። ልቤ በእውነትህ የጸና ነው፤ ከአንተ ዘንድ ያልሆነውን ሃሳብ፣ ድምጽ እና ተጽእኖ እለያለሁ። የቃልህ እውቀት ይመራኛል፣ ሁል ጊዜም ከፈቃድህ ጋር የሚስማማ ንግግርን እናገራለሁ። በድል እመላለሳለሁ፣ በክርስቶስ በሆንኩት ማንነቴ ንቃተ-ህሊና እኖራለሁ። ሃሌሉያ!

ለተጨማሪ ጥናት
├─ ቆላስይስ 3፡2
├─ ሮሜ 8፡5
├─ ኢሳይያስ 55፡ 8-9
└─

━━━━//━━━

19/05/2026

RHAPSODY OF REALITIES
(Amharic) 🇪🇹🇪🇹🇪🇹

Tuesday 19 , May 2026
ማክሰኞ፣ ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም

📜ሁልጊዜም ፈቃዱን ይጠብቃል
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

📖አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በሴራ አንድ ነው ብለው ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም። አቤቱ፥ የአኪጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጥ እለምንሃለሁ አለ (2ኛ ሳሙኤል 15:31)

👤 ፓስተር ክሪስ
════════
በቀድሞ ጥናታችን፣ የዳዊት ልጅ አቤሴሎም፣ እንዴት በአባቱ ላይ ጠንካራ አመፅን እንደመራ ጠቅሰን ነበር። አኪጦፌል ከእግዚአብሔር የሚናገር ሰው እንደሚከበር ያክል የተከበረ ነበር፣ ነገር ግን በዳዊት ላይ አመፁን የበለጠ በማፋፋም ከአቤሴሎም ጎራ ተቀላቀለ። ከዚህ የተነሳ፣ ዳዊት የአኪጦፌልን ጥበብ ወደሞኝነት እንዲቀይርለት ወደ ጌታ ጸለየ።

የዳዊት ጸሎት አንዳች አስደናቂ ነገር አስከተለ። ዳዊት ለእግዚአብሔር ወደሚያመልከበት ተራራ ራስ ሄደ፣ በዚያም አርካዊው ኩሲ
ሊገናኘው እንደመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። የእግዚአብሔር መልስ ስትራቴጂካዊ ቦታ ሊይዝ ባለው ሰው መልክ ተገልጦ መጣ።

ዳዊት ወዲያው ያ ምን ማለት እንደነበርና ምን ማድረግ እንደነበረበት ተረዳ። ኩሲ ወደከተማ እንዲመለስና እሱን (ዳዊትን) እንዳገለገለ፣ ራሱን ለአቤሴሎም አገልጋይ አድርጎ እንዲያቀርብ ነገረው። አላማው ግልፅ ነበር፤ ኩሲ ይህን በማድረጉ በአቤሴሎም ሰፈር ሆኖ የአኪጦፌልን ምክር የሚቃወምበትና የሚያሸንፍበት ስፍራ ላይ እንዲሆን ነበር።

ይህ እግዚአብሔር እቅዱን እንዴት እንደሚያስጠብቅ የሚያስታውቅ አስደናቂ ማሳያ ነው። በተንኮለኛ አማካሪዎች አማካኝነት ሰይጣናዊ ስትራቴጂዎች በሚነሱበት ጊዜ እንኳን እግዚአብሔር እነዚያን ወጥመዶች ከንቱ የሚያደርጉና የሚያፈርሱ የእርሱ የራሱ የጥበብና የጽድቅ መሳሪያዎች የሆኑ ህዝቦች አሉት።

ስለዚህ፣ መሪ ከሆናችሁ፣ ውሳኔዎቻችሁን የሚያውቁና በዚያም ላይ ተፅእኖ ማሳደር የሚችሉ፣ በካቢኔያቸሁ ወይም በውስጥ ዙሪያችሁ ያሉት ሰዎች ማንነት ተፅእኖ እንዳለው ማወቅ ያስፈልጋችኋል። የእግዚአብሔር እቅድ እንዲያይልና በአለማችን ላይ ማሸነፉን እንዲቀጥል የሚያደርጉ፤ ለጽድቅና ለእውነት ድምፅ ሆነው የሚቆሙ ሊሆኑ ይገባቸዋል።

እግዚአብሔር፣ በጥበቡ፣ ሁልጊዜም የእርሱ "ኩሲ" የሆኑ፣ ክፉ ምክሮችን ከንቱ የሚያደርጉና የእግዚአብሔር ፈቃድ መፈፀሙን የሚያረጋግጡ፣ በመንፈስ ቅዱስ ወደ ስፍራው የመጡ ወንዶችና ሴቶች በሃገራት መሪዎች መካከል አሉት። ጽድቅን እንዲጠብቁና በሃገራት ላይ ያለውን እቅድ ለማስፋፋት እንዲረዷቸው ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ እርሱ ያስቀመጣቸውን ወንዶችና ሴቶች ለይተው ያውቋቸው ዘንድ ሁልጊዜ ለመሪዎች ጸልዩ። ሃሌሉያ!



ጸሎት
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ውድ አባት ሆይ፤ ልጆችህ የወንጌልህን እውነት አፅንተው ሲይዙና ጽድቅን በአለም ዙሪያ ሲመሰርቱ የአንተ ጥበብና ጽድቅ በሃገራት ላይ አይሎ ይገለጣል። የአንተ ፈቃድ በምድር ላይ ይፈፀማል፤ ግዛትህም ሳይገደብ ይስፋፋል፤ በኢየሱስ ስም። አሜን።

ለተጨማሪ ጥናት
├─ መጽሐፈ ምሳሌ 21:30
├─ ትንቢተ ኢሳይያስ 8:10
├─መጽሐፈ ኢዮብ 5:12
└─

━━━━//━━━

Want your place of worship to be the top-listed Place Of Worship in Addis Ababa?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Telephone

Website

Address


Summit 72
Addis Ababa
1000