Awash Subah brodcast

Awash Subah brodcast

Share

I was born to be Ethiopian, I am Ethiopian, I will die for Ethiopia! ! ! I love my beloved country Ethiopiyaye! !!

Photos from Awash Subah brodcast's post 08/04/2024

የ ቬትናም ጦርነት (The vietnam war)
“ልዕለ ኃያሏ” ሀገር አሜሪካ ሽንፈትን ቀምሳ ከወጣችበት ጦርነቶች መካከል በታሪክ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። የቬትናም ጦርነት! ይህ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ክቡር የሰው ልጅን ህይወት ያስገበረው ጦርነት፣ አፍጋኒስታን ላይ እንደታየው አሜሪካ በመጨረሻ ማለቂያ የሌለውን ጦርነት ጥላ እንድትሸሽ እንድትወስን ያስገደዳት ጦርነት ነበር። ያውም ሃምሳ ስምንት ሺህ ወታደሮቿን በሞት ተነጥቃ። አሜሪካ ቬትናምን ለቃ የወጣችው በፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ውሳኔ እ.አ.አ በ1973 ዓ.ም. ነበር።

#ጦርነቱ እንዴት ተጀመረ?
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በደቡብ ምስራቅ ኢሲያ በኢንዶቻይና ባሕረሰጤ የምትገኘው ሀገር ቬትናም በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር ነበረች። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግዜ ጃፓን ቬትናምን ስትወር በቻይና እና በሶቪዬት ህብረት ኮሚኒስት ርዕዮት መንፈስ የነቃው የቬትናሙ ሆ ቺ ሚኒ ሀገሩን ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ብሎም ከጃፓን ወረራ ነጻ ለማውጣት የሀገሩን ልጆች አስተባብሮ ተነሳ። የዚህ አብዮተኛ ስም በኢትዮጵያ የተማሪዎች ትግል ውስጥ ሲጠቀስ የምንሰማበትም ምክንያት አልበገር ባይነቱ ነው።
ፋኖ ተሰማራ

ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆ ቺ ሚኒ

እንደ ቼ ጉቬራ!

ጃፓን ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ ጦሯን ከቬትናም ብታስወጣም በBao Dai የሚመራ የሞግዚት አስተዳደር በቬትናም አስቀምጣ ነበር። በሆ ቺ ሚኒ የሚመራው ኃይል ግማሹን ቬትናም ሲቆጣጠር የጃፓኑ የሞግዚት አስተዳደር ደግሞ የተቀረውን በመያዝ መላውን ቬትናም አንድ አድርጎ ለመግዛት የሚደረገው ፍጥጫ ቀጠለ። የሁለቱ መሪዎች መሰረታዊ ልዩነት የርዕዮተ ዓለም ነበር። ሆ ቺ ሚኒ ኮሚኒስት ቬትናምን የመመስረት ሃሳብ የሰነቀ ሲሆን ፣ በተቃራኒው ፈረንሳይ የተማረው ባኦ ዳይ ሀገሩን በምዕራባዊያኑ ሞዴል የመገንባት ዓላማ ነበረው። የአንድ ሀገር ልጆች ግን ሁለት የሚቃረኑ የፖለቲካ አመለካከቶች! በዚህም ምክንያት ቬትናም ደቡብ እና ሰሜን ተብላ ለሁለት ተከፈለች።

እዚህ ጋር ነው እንግዲህ አሜሪካ የምትመጣው። ቀዝቃዛው ጦርነት እየተፋፋመ ሲመጣ የአሜሪካው የወቅቱ ፕሬዝዳንት Dwight D. Eisenhower ማንኛውም ከሶቪዬት ህብረት ጋር የተባበረን ኃይል በጠላትነት በመፈረጅ ድጋፋቸውን ለደቡብ ቬትናም እንደሚሰጡ ተናገሩ። አሜሪካ በጊዜው Bao Daiን ከስልጣን በማስወገድ (በምርጫ?) የሰሜን ቬትናምን ስልጣን ለተቆጣጠረው Ngo Dinh Diem የስልጠና እና የመሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን ቀጠለች። የሰሜኑ ኃይልም viet cong እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት እና በሆ ቺ ሚኒ ይመሩ የነበሩት ኮሚኒስት ኃይል ላይ ከፍተኛ ጫና እና ጥቃት ማድረስ ጀመረ። ይሁንና viet cong በቀላሉ የሚፈታ ኃይል ሊሆን አልቻለም።

#የልዑኩ ምክር
እ.አ.አ በ1961 ዓ.ም. የቬትናምን ሁኔታ ገምግሞ ሪፖርት እንዲያደርግ የተላከው ልዑክ ወደ አሜሪካን ሲመለስ ለፕሬዝዳንት ኬኔዲ ያቀረበው ሃሳብ ሰፋ ያለ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ያካተተ ነበር። ይሁንና ኬኔዲ ወታደራዊ እርዳታው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቢወስኑም የአሜሪካን ወታደር በብዛት ወደ ቬትናም የመላኩ ጉዳይ ላይ ብዙም አልገፉበትም። በኬኔዲ ዘመን በቬትናም የነበረው የአሜሪካ ወታደር ቁጥርም ከአስር ሺህ ያነሰ ነበር።

በ1963 ዓ.ም. Ngo Dinh Diem በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ሲወርዱ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲም በተተኮሰባቸው ጥይት ተገደሉ። የኬኔዲን ሞት ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት Lyndon B. Johnson የአሜሪካን ጦር በቬትናም ወደ ለየለት ጦርነት እንዲገባ አደረጉት።
#በ1965 ዓ.ም. 82,000 የአሜሪካን ወታደሮች በቬትናም ጦርነት ቢዘምቱም ጦርነቱን ማሸነፍ ግን አልቻሉም። ይልቁንም በቬትናም የነበሩ የጦር መሪዎች ጦርነቱን ለማሸነፍ ተጨማሪ 175,000 ወታደር ያስፈልገናል ሲሉ የአሜሪካን መንግስት ጠይቀዋል። በሀገረ አሜሪካ ጦርነቱን የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች ኣየበረቱ ቢመጡም ፕሬዝዳንት ጆንሰን ከገቡበት ጦርነት ያወጣናል ብለው በማሰብ በሁለት ዙር 200,000 የአሜሪካን ወታደሮች ወደ ቬትናም እንዲዘምት ትዕዛዝ ሰጡ።

በ1967 ዓ.ም. ገደማ በቬትናም የነበርው የአሜሪካ ወታደር ቁጥር ወደ 500,000 ቢጠጋም ይህ ነው የሚባል ድል ግን ማስመዝገብ አልቻለም ነበር። አሜሪካ ከምታስመዘግበው ድል ይልቅ በየዕለቱ በየጦር ግንባሩ የሚወድቅ ወታደሯን ማንሳት እና መቁጠር ሆነ ዜናው ሁሉ። ይህን የሰሙ አሜሪካዊያን ልጆቻችንን መልሱልን፣ ቬትናምን ለቬትናማዊያን ተውላቸው፣ ከቬትናም ውጡ ሲሉ አደባባይ ወጡ።

ቀጣዮቹ የጦርነት ዘመናት ለአሜሪካን ወታደሮች በአካል እና በስነ ልቦና የተጎዱባቸው ግዜዎች ነበሩ። አብዛኛው ወታደር ለስነ ልቦና ቀውስ ሲዳረግ አያሌዎቹ ደግሞ አደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎች ሆኑ፣ ለpost-traumatic stress disorder ተጋለጡ።


ፕሬዝዳንት ኒክሰን ወደ ስልጣን ሲመጡ የቀደመውን አስተዳደር በመውቀስ የአሜሪካን ወታደር ከቬትናም ለማውጣት እና በምትኩ የደቡብ ቬትናም ኃይሎች ራሳቸውን ችለው እንዲዋጉ ለማድረግ ውሳኔ ውሳለፉ። የዚህ እስትራቴጂ መጠሪያ ነበር Vietnamization!

“In the previous administration, we Americanized the war in Vietnam. In this administration, we are Vietnamizing the search for peace.”

#የመጨረሻዎቹ ቀናት

እንደ አውሮፓዊያኑ ዘመን አፕሪል 30 ቀን 1975 ዓ.ም Saigon በ ቬትኮንጎች እጅ ስትወድቅ የመጨረሻዎቹ አሜሪካዊያን ቬትናምን እየለቀቁ ነበር። ይህ ዕለት የቬትናምን ጦርነት ፍጻሜ ያበሰረ ዕለት ቢሆንም ለአሜሪካዊያን እድሜ ዘመናቸውን የማይፍቁት የስንፈት ታሪክ በዓለም የታሪክ መዝገብ ላይ የተፋቀበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለት የአሜሪካ መንግሥት በቬትናም የቀሩ ዜጎቹን ኣና ወታደሮቹን በጥድፊያ በአየር ማጓጓዣዎች ለማውጣት ያደርግ የነበረው ሙከራ እና ጦርነቱን ሽሽት ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ይሞክሩ የነበሩት የቬትናማዊያን የሞት ሽረት ትግል ትዕይንት መቼም ቢሆን ከህሊና የሚጠፋ አይደለም።

Photos from Awash Subah brodcast's post 15/12/2023

#“በአፍሪካ የራሱ የጣት ምልክት ያለው #የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ”
☆☆☆☆▪▪▪▪▪☆☆☆☆☆
“በምልክት ቋንቋ የሚነጋገሩ ሰዎች ሲያዩ የሚያማትቡ፣ ደንግጠው የሚሸሹም ብዙዎች ናቸው” የሚለው የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እና ጋዜጠኛው አማረ አያሌው ነው።
ስለ ምልክት ቋንቋ እንዲሁም መስማት ስለተሳናቸው ሰዎች በብዙዎች ዘንድ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ቋንቋውን እንደ ቋንቋ ለመውሰድ የሚቸግራቸው ጥቂት አይደሉም።
አማረ ግን “የኢትዮጵያ 81ኛው ቋንቋ” ይለዋል።
በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ምሥረታ ውስጥ ካሉ አንዱ የሆኑት አቶ ተክለሃይማኖት ደርሶ እንደሚሉት፣ በዚህ የተዛባ አመለካከት ሳቢያ ማኅበረሰቡ መስማት የተሳናቸውን ‘ራሳቸውን ችለው መኖር የማይችሉ ደካሞች’ አድርጎ ይወስዳል።
ቋንቋ ያላቸው፣ የሚግባቡ አድርጎ አለመውሰድም አለ።
ሆኖም ግን “ቋንቋ አላቸው። ቋንቋ ካለ ደግሞ ባህል አለ። ባህል ካለ ደግሞ ኩራት አለ። የማንነት ክብር ስሜት አለ” ይላሉ።
ከታዋቂ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች አንዷ እስከዳር ይኩኖአምላክ እንደምትለው፣ ካለው የግንዛቤ እጥረት የተነሳ በሌሎች አገራት የምልክት ቋንቋ ያለው ተደራሽነት በኢትዮጵያ እምብዛም አይስተዋልም።
የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ብንመለከት ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ዚምባብዌን ጨምሮ 41 አገራት የምልክት ቋንቋን ብሔራዊ ቋንቋቸው አድርገዋል።
የመስማት የተሳናቸው ዩኒቨርስቲዎችም ተጠቃሽ ናቸው።
በተለያየ ዕድሜ ላሉ ሰዎች የተዘጋጁ የምልክት ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት እና መዝገበ ቃላትም ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ በ1960ዎቹ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ከተመሠረተ በኋላ ነው መዝገበ ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው።
ይህ ዘገባ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን እንዲሁም የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላትን ይዳስሳል።
■‘መስማት የማትችል ከሆንክ እንዴት ልትማር ነው?’
አቶ ተክለሃይማኖት ደርሶ በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ምሥረታ ውስጥ ካሉ መካከል አንዱ ናቸው።
በ1963 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ “መስማት የማትችል ከሆንክ እንዴት ልትማር ነው?” መባላቸውን ያስታውሳሉ።
ይህንን የተዛባ አመለካት ከግንዛቤ እና ከመረጃ ክፍተት ጋር ያስተሳስሩታል።
በምልክት ቋንቋ ረገድ፣ ከሌሎች አገራት አንጻር ሲታይ “እኛ ገና ዳዴ የምንል ጀማሪዎች ነን” ይላሉ።
ለምሳሌ በአሜሪካ መስማት የተሳናቸው ዩኒቨርስቲ የሆነው ጋሎዴት የተከፈተው ከ159 ዓመት በፊት ነው።
በአፍሪካ ውስጥ በደቡብ አፍሪካ የተሻለ ተሞክሮ እንዳለ ይነገራል።
“በቅርብ ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምልክት ቋንቋ እና መስማት የተሳናቸው ባህል መጠናት መጀመሩ ተስፋ ሰጭ ነው” ይላሉ አቶ ተክለሃይማኖት።
በቀደሙት ዓመታት መስማት የተሳናቸው እንደ አሁኑ በአደባባይ በምልክት ቋንቋ ለመነጋገር አይደፍሩም ነበር።
“ያለ ምንም መሸማቀቅ ሽንጣቸውን ገትረው በምልክት ቋንቋቸው የሚነጋገሩበት ጊዜ አልነበረም። መንገድ ላይ እየሄዱ ሳለ ሰው ሲቀርባቸው፣ እስኪያልፍ ድረስ ንግግራቸውን ገታ ያደርጉ ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ።
በዚያ ወቅት የነበረውን ሁኔታ አቶ ተክለሃይማኖት ሲገልጹ “. . .እንዲያውም መስማት የተሳናቸው ‘ደናቁርት’ እየተባሉ የሚጠሩበት ጊዜም ነበር። በወቅቱ በመንግሥት የተቋቋመ አንድም መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት አልነበረም” በማለት ነው።
*ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ወቅት ከኖርዲክ አገራት እና ከአሜሪካ በመጡ ሚሲዮናውያን የተቋቋሙ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ሁለት እና በከረን ደግሞ አንድ ነበሩ።
ያኔ በአዲስ አበባ የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ በኤርትራ ደግሞ የኖርዲክ የምልክት ቋንቋ ነበር የሚጠቀሙት።
በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል መስማት የተሳናቸው ለመግባባት የሚጠቀሙበት ቋንቋ ወጥነት ባለው ሁኔታ የምልክት ቋንቋ ሆኖ የተጀመረው ሚሲዮናውያን ትምህርት ቤት ከከፈቱ በኋላ መሆኑን ያስረዳሉ።
መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር በ1963 ዓ.ም. እስከሚመሠረት እንዲህ ቆይቷል።
ማኅበሩ ሲመሠረት ከትምህርት ቤት በዘለለ መስማት የተሳናቸው የሚገናኙበትም ሆነ።
“ያኔ በኢትዮጵያ የፊደል የጣት ምልክት አልነበረም” ይላሉ አቶ ተክለሃይማኖት።
ከዚያም የማኅበሩ ሦስት መሥራቾች ያዘጋጁት የጣት ምልክት በ1967 ዓ.ም. ለያኔው የትምህርት ሚኒስትር ቀረበ። በትምህር ቤቶች ጥቅም ላይ እንዲውልም ተፈቀደ።
በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ከመዘጋጀቱ በፊት አብዛኛው የማኅበረሰቡ ክፍል “መስማት የተሳናቸው መማርም ሆነ መሥራት ይችላሉ ብሎ የማያስብበት ጊዜ ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ።
■‘መዝገበ ምልክት’
አቶ ተክለሃይማኖት የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት ከሚለው ይልቅ ‘መዝገበ ምልክት’ የሚለውን አገላለጽ ይመርጣሉ።
እንደ ማንኛውም ቋንቋ ተሰንዶ መዘጋጀቱ ለጥናት እና ለምርምር እንዲሁም ቋንቋውን መማር ለሚፈልጉ ይረዳል ይላሉ።
“መዝገበ ምልክቱ መኖሩ መስማት የተሳናቸው የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው፣ ባህል ያላቸው አድርጎ እንዲመለከት ያግዛል” በማለት ነው የሚያስረዱት።
“ቋንቋ ካለ ባህል አለ። ባህል ካለ ደግሞ ኩራት አለ። የማንነት ክብር ስሜት አለ። ማንም በራሱ ቋንቋ ሲያናግሩት ደስታ እንደሚሰማው ሁሉ፤ መስማት የተሳናቸውም በራሳቸው ቋንቋ የሚያናግራቸው ሲያገኙ ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል። ለተናጋሪውም ትልቅ አክብሮት ይሰጣል።”
ሆኖም የምልክት ቋንቋ፣ ቋንቋ መሆኑን የማይገነዘቡ እንዳሉ ይናገራሉ።
በአንድ ወቅት የልጃቸው አስተማሪ ምልክት ቋንቋ ‘ቋንቋ’ አይደለም ማለቱን ልጃቸው እንዴት በብስጭት እንደነገራቸው እና በነገታው ስለ ቋንቋው አስረጂ ጽሑፎች ይዘው ለትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር መስጠታቸውን አይረሱትም።
እንደ ማንኛውም ቋንቋ ‘መዝገበ ምልክት’ መኖሩ፣ በቴክኖሎጂ ዕድገት ምክንያት የሚፈጠር የባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥን ተከትሎ ከጥቅም ውጪ የሚሆኑ ቃላት እንዳይረሱ ለማድረግም ይረዳል ይላሉ።
በየጊዜው የሚፈጠሩ አዳዲስ ምልክቶች በመጽሐፍት ተሰንደው መካተት እንዳለባቸውም ያክላሉ።
■‘81ኛው የኢትዮጵያ ቋንቋ’
አማረ አያሌው የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እና ጋዜጠኛም ነው። በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት ፕሮጀክት ውስጥ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እና አስተባባሪም ነው።
“አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ መስማት የተሳናቸው የሚጠቀሙበት ቋንቋ እንደመሆኑ ተሰንዶ መቀመጡ እንደ ቅርስ ነው” ሲል ነው መዝገበ ቃላቱን የሚገልጸው።
የመጀመሪያው ‘ሀ’ የተባለው መጽሐፍ የታተመው በ1960ዎቹ ነበር። በቀጣይ ‘ለ’ የሚል መጽሐፍም ታትሟል። ከዚያም በተለያዩ ዓመታት ለምሥራቅ እና ለደቡብ አፍሪካ አገራት ድጋፍ ሲሰጥ መዝገበ ቃላት ታትመዋል።
በቅርቡም ከፊንላንድ በተሰጠ ድጋፍ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት ታትሟል።
መጽሐፉ በፎቶ የምልክት ቋንቋ ምልክቶችን የሚያሳይ ነው። 2500 ፎቶዎች እና 1300 ምልክቶች የያዘ ነው።
“በምልክት ቋንቋ ለመግባባት አቅጣጫ፣ እንቅስቃሴ፣ የፊት አገላለጽ፣ ምልክት የሚደረግበት የሰውነት ክፍል በዚህ መጽሐፍ ተካተዋል” ሲል ነው አማረ የሚገልጸው።
መጽሐፉ በዋናነት መስማት ለተሳናቸው፣ መስማት ለተሳናቸው ቤተሰቦች እና ለሕዝብ አገልግሎት ሰጪዎችም እንደሚረዳ ይናገራል።
“መስማት ከተሳናቸው ጋር ለመግባባት ያግዛል። አካታችነትን ያረጋግጣል። ቋንቋውንም ከትውልድ ትውልድ ያሻግራል” ይላል።
ይህንን መጽሐፍ የክልል ዩኒቨርስቲዎች እና የመንግሥት ተቋማት ለማከፋፈል መሞከራቸው ፍላጎቱ እንዳለ ቢያሳይም ውስንነቱ ግን እንዳለ ነው።
‘81ኛው የኢትዮጵያ ቋንቋ’ በማለትም ነው አማረ የሚጠራው።
ይህ ምልክት በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ 'ጨዋታ' ማለት ነው
የየአገሩ የምልክት ቋንቋ የተለያየ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም የተለየ የምልክት ቋንቋ አለ።
በሌሎች አገራት የምልክት ቋንቋን የሕክምና እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎችም ይማራሉ።
አሜሪካንን እንደ ምሳሌ ብናነሳ የምልክት ቋንቋ ሦስተኛ በስፋት የሚነገር ቋንቋ ነው።
“የራሱ የሆነ የጣት ምልክት ያለው የአፍሪካ ቋንቋ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ነው። ግን አልተነገረለትም” ይላል አማረ።
በዓመታት ሂደት ስለ ምልክት ቋንቋ ያለው ግንዛቤ መሻሻሉ ባይካድም አሁንም ክፍተቶች መኖራቸው እሙን ነው።
“. . .መስማት የተሳናቸው ባህል ላይ ጥናት ሳደርግ በ13ኛው ክፍለ ዘመን መስማት የተሳናቸው ለመሰባሰብ መሞከራቸውን የሚያሳይ መረጃ ሁሉ አግኝቻለሁ” ሲል አማረ ይናገራል።
ማኅበረሰባዊ ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባም ያክላል።
“ካለው የአመለካከት ክፍተት የተነሳ የምልክት ቋንቋ ሲያዩ የሚያማትቡ፣ ደንግጠው የሚሸሹም አሉ” የሚለው አማረ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቭዢን በምልክት ቋንቋ ዜና መተላለፍ ከጀመረ በኋላ ለውጥ መታየቱን ያስታውሳል።
በብሔራዊ ቴሌቪዥን መታየት ከጀመረ በኋላ እንደ መደበኛ መግባቢያ ቋንቋ መታየት እንደጀመረም ይናገራል።
የምልክት ቋንቋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መሰጠት መጀመሩ እና በመስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበርም ሥልጠናዎች መዘጋጀቱ የመሻሻሉ አካል አድርጎ ነው የሚወስደው።
ሆኖም ግን መስማት የተሳናቸውን ማግለል አሁንም መሰናክል ነው።
“መሥራት እየቻሉ መሰናክሎች ስለበዙባቸው ከሥራ ውጪ ይሆናሉ። መስማት የተሳናቸው በቋንቋቸው ተምረው መሥራት የሚችሉበት መንገድ መመቻቸት ያለበት ለዚህ ነው።”
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ከተመሠረተ 52 ዓመታት ቢያስቆጥርም የገንዘብ እና የሰው ኃይል ውስንነቱ እንዳለ ነው። ማኅበሩን ማጠናከር የራሱ ሚና እንደሚኖረው አማረ ያምናል።
በኢትዮጵያ ቋንቋው እንዲስፋፋ መስማት የተሳናቸው እንዲሁም የተቀረው ማኅበረሰብ ተካታችነትንም እንደሚያሻ ያክላል።
“የምልክት ቋንቋ በማስተርጎሜ በጣም ደስተኛ ነኝ”
በኢቢሲ የምልክት ቋንቋ ክፍል የምትሠራው እስከዳር ይኩኖአምላክ በአገሪቱ ከታዋቂ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች መካከል አንዷ ናት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2002 ዓ.ም. የምልክት ቋንቋ ትምህርት ክፍል ገብታ ከተማረች በኋላ ኢቢሲን ጨምሮ በሌሎችም መድረኮች በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚነት ሠርታለች።
የዩኒቨርስቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለች ጀምሮ ላለፉት 10 ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥም በአስተርጓሚነት እየሠራች ትገኛለች።
አሁን ያለችበት ከመድረሷ በፊት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለች በዓመቱ ትምህርት ክፍል ልቀይር ይሆን? እያለች ታስብ እንደነበር ታስታውሳለች።
“የምልክት ቋንቋ ትምህርት ክፍል ሲደርሰኝ እንዴት እንደምማር እና እንደምግባባ ፈርቼ ነበር” ትላለች።
ቆይታ ግን ሐሳቧን ለወጠች። “ነገር ግን የምልክት ቋንቋን ቶሎ ነበር የቻልኩት። ዶርም ውስጥም ሰባት መስማት የተሳናቸው ከእኔጋ ነበሩ። ከእነሱ ጋር ስውል ሳድር ቋንቋውን ቻልኩ።”
በሌሎች አገራት ቋንቋው ካለው ተደራሽነት አንጻር የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ውስነት አንደኛው ምክንያት የግንዛቤ እና የዕውቀት አለመኖር መሆኑን እስከዳር ትናገራለች።
“የሥራ ዘርፍን ብንመለከት እንኳን ከ70 በመቶ ያላነሱት መስማት የተሳናቸው በእንጨት ሥራ ይሰማራሉ። በሙያው ውጤታማ ቢሆኑም በሌሎች ዘርፎች ተቀጥረው ለመሥራ ሲሞክሩ የሚቀጥራቸው ስለማይኖር ነው አንድ ሙያ ብቻ የሚመርጡት” ትላለች።
መስማት የተሳናቸውን ሥራ መቅጠር አብሮ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ መቅጠር እንደሚያስፈልገው በማሰብ ተቋማት ለመቅጠር እንደማይፈቅዱ ትናገራለች።
መስማት የተሳናቸው ‘አይችሉም’ በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በተለያዩ መድረኮች ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚገፉም እስከዳር ትጠቅሳለች።
ለዚህም ነው የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት አስፈላጊነትን አጽንኦት የምትሰጠው።
የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት መኖሩ አንዳንድ ከረዥም ጊዜ በኋላ የሚዘነጉ ወይም የሚጠፉ የምልክት ቋንቋዎች እንዳይረሱም አስተርጓሚዎችን ይረዳል ትላለች።
ሆኖም መዝገበ ቃላቱ ተደራሽነቱ ውስን እንደሆነ ሳትገልጽ አታልፍም።
መስማት ከተሳናቸው ትምህርት ቤቶች እና የአካል ጉዳተኞች መገልገያዎች ከሚሸጡ መደብሮች በዘለለ አይስተዋልም።
እንደ ሌሎች የአካል ጉዳቶች በዕይታ የማይለይ መሆኑ መስማት የተሳናቸውን በተለየ ሁኔታ የሚፈትን እንደሆነ እና በምልክት ቋንቋ በቂ መረጃ አለመቅረቡም ሌላ ክፍተት እንደሚፈጥር ታስረዳለች።
ኮቪድ-19 በተነሳበት ወቅት ስለ ወረርኙ መረጃዎች በምልክት ቋንቋ አለመዘጋጀታቸው መስማት የተሳናቸውን ለሕመሙ ተጋላጭ አድርጎ እንደነበር ታስታውሳለች።
“በዚያ ወቅት ከእሑድ እስከ እሑድ በዜና ሽፋን ስሰጥ ነበር። በሥራዬ ለውጥ ካመጣችሁባቸው አንዱ ይሄ ነው” ትላለች።
“በብዛት ያለው አመለካከት የምልክት ቋንቋ ብንማርስ ባንማርስ የሚል የሚል ነው” ስትል እስከዳር ትናገራለች።
እሷ ግን “የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላ ነው የምትገልጸው።
bbc

Want your public figure to be the top-listed Public Figure in Awash?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Category

Address


Awash Town
Awash